ሚያዝያ 9 2017 - የሜትር ታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ''ያንጎ'' አሽከርካሪዎቹ የሙሉ አረቦን ፕሪሚየም ኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊያደርግ ነው፡፡
- sheger1021fm
- 3 days ago
- 1 min read
የሜትር ታክሲ አገልግሎት አቅራቢው ''ያንጎ'' አሽከርካሪዎቹ የሙሉ አረቦን ፕሪሚየም ኢንሹራንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ሊያደርግ ነው፡፡
ለዚህም ሲል ያንጎ ከንብ ባንክ እና ንብ ኢንሹራንስ ጋር የሦስትዮሽ ሥምምነት በዛሬው እለት ተፈራርሟል።
ስምምነቱ በሕግ የተቀመጠውን አስገዳጅ የሦስተኛ ወገን ሽፋን የከፈሉ የያንጎ አሽከርካሪዎች ተጨማሪ የአረቦን ኢንሹራንስ ተጠቃሚ የሚሆኑበትን ዕድል ይሰጣል ተብሏል፡፡
ሥምምነቱም የሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ብቻ የነበራቸውን የያንጎ አሽከርካሪዎች ሙሉ የኢንሽራንስ ክፍያ ለንብ ኢንሹራንስ እንዲከፈል የሚያደርግ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ያንጎን የሚያስተዳድረው ''ጂቱጂ አይቲ ሶሉሽን'' በኢትዮጵያ ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ቴዎድሮስ መሃሪ " የሦስትዮሽ ስምምነቱ የያንጎ አሽከርካሪዎች የሚያጋጥማቸውን ወሳኝ ፈተና በመቅረፍ ተመጣጣኝ እና ተደራሽ የሆነ አጠቃላይ የመኪና ኢንሹራንስ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማድረግ ታስቦ የተዘጋጀ ነው" ብለዋል።
"በአሁኑ ጊዜ አብዛኛው የያንጎ አሽከርካሪዎች ለተሸከርካሪዎቻቸው ጥበቃ በሦስተኛ ወገን ኢንሹራንስ ብቻ ይተማመናሉ" ያሉት አቶ ቴዎድሮስ፤ በዚህም ምክንያት አደጋ በሚደርስበት ወቅት ዋና የገቢ ምንጫቸውን ለጥገና በማውጣት ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን ለችግር የሚዳርጉበት አጋጣሚ መኖሩን አንስተዋል።

በመሆኑም የዛሬው ሥምምነት አሽከርካሪዎች በአንድ ጊዜ ሳይሆን በየወሩ አረቦን መክፈል የሚችሉበትን ዕድል የፈጠረ በመሆኑ፤ አሽከርካሪዎች ላይ የሚደርሰውን የገንዘብ ጫናን በእጅጉ ይቀንሳል ተብሎ እንደታመነበት ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም የአረቦን ክፍያውን ከአሽከርካሪዎች ጉርሻ (ቦነስ) ላይ በቀጥታ መቀነስ የሚያስችል አሰራር በመዘርጋቱ፤ አሽከርካሪዎች የአረቦን ክፍያቸውን ከሚያገኙት ጉርሻ ተቀናሽ በማድረግ መፈጸም ያስችላቸዋል ብለዋል፡፡
በዚህም ምክንያት በሚያገኙት አጠቃላይ ሽፋን አሽከርካሪዎች ለተሽከርካሪዎቻቸው ጥበቃ እንዲሁም ለቤተሰቦቻቸው መረጋጋት ይሰጣቸዋል ሲሉም አስረድተዋል።
በጂቱጂ አይቲ ሶሉሽን ሥር የሚተዳደረው ዓለም አቀፉ የሜትር ታክሲ አገልግሎት ሰጪ ያንጎ በኢትዮጵያ አገልግሎት መስጠት የጀመረው ከህዳር ወር 2016 ዓ.ም ጀምሮ ነው፡፡
ንጋቱ ሙሉ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Telegram; https://t.me/ShegerFMRadio102_1
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
📌Spotify : https://shorturl.at/QG8f2
Kommentare