ሱዳን ከኢትዮጵያ በቀን የምትወስደው የኤሌክትሪክ ኃይል ከ2 መቶ ሜጋዋት ወደ 50 ሜጋዋት ወርዷል ሲል የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ተናገረ፡፡
ጦርነት ውስጥ ያለችው ሱዳን ከኢትዮጵያ የምትወስደው የኤሌክትሩክ ኃይል በእጅጉ መቀነሱን ተነግሯል፡፡
ሱዳን ጦርነት ውስጥ ከመግባቷ በፊት ከኢትዮጵያ የምትገዛው የኤሌክትሪክ ኃይል በቀን እስከ 2 መቶ ሜጋዋት የነበረ ሲሆን አሁን ግን 50 ሜጋዋትና ከዚያ በታች ሆኗል ሲል አገልግሎቱ አስረድቷል፡፡
በአገልግሎቱ የስትራቴጂ እና ኢንቨስትመንት ዳይሬክተር የሆኑት ወንድወሰን ተሾመ ለሱዳን የሚቀርበው የኤሌክትሪክ ኃይል በእጅጉ መቀነሱን ለሸገር ነግረዋል፡፡
ዳይሬክተሩ ለሱዳን የሚቀርበው ኃይል ከመውረዱም በላይ ለተጠቀሙት የኤሌክትሪክ ኃይል እየከፈሉ አይደለም ያሉ ሲሆን ይሁንና በሁለቱ ሀገራት መካከል በታሰረው ውል መሰረት ለተጠቀሙበት ካልከፈሉ አገልግሎቱን ማቋረጥ የሚቻል ቢሆንም ግንኙነቱ እንዳይሻክር ኢትዮጵያ ይህንን አላደረገችም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ከሱዳን ከጅቡቲና ከኬኒያ የኃይል ትስስር ያላት ሲሆን በቀን እስከ ሁለት ቴራ ዋት ሀወር ለሶስቱ ሀገራት ኃይል እንደምታቀርብ አገልግሎቱ ጠቁሟል፡፡
ከፍተኛ ፍላጎት እና አለመረጋጋት የሚታይበትን የአፍሪካ ቀንድ በኃይል የማስተሳሰር ስራ እየተሰራ እንዳለ የውሃ እና ኢነርጂ ሚንስቴር ተናግሯል፡፡ኢትዮጵያ ያላት የሀይል ሀብት 150 ጊጋዋት ይሆናል የተባለ ሲሆን በአቅም ማነስ እስካሁን ማመንጨት የቻለችው ግን 5.4 ጊጋ ዋት ነው ተብሏል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ ይህንን ይጫኑ…
ያሬድ እንዳሻው
Comments