top of page

ሰኔ 27፣ 2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

በኬንያ የፓርላማ አባላትን ጨምሮ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት ሹሞች ተፈቅዶ የነበረው የደሞዝ ጭማሪ እንዲቀር ተደረገ፡፡

 

ቀደም ሲል ጭማሪው ካለፈው ሰኞ አንስቶ ስራ ላይ ይውላል ተብሎ እንደነበር ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

ጭማሪው አዲሱን የፋይናንስ ህግ ታሳቢ አድርጎ የተሰላ ነበር ተብሏል፡፡

 

ህጉ ታክስ በመቆለል ኑሯችንን ይበልጥ ያከብድብናል ያሉ ዜጎች ግጭት ያስከተለ ተቃውሞ ካበረቱበት በኋላ መቅረቱን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

ይሄን ተከትሎም ፕሬዘዳንት ዊሊያም ሩቶ የፓርላማ አባሎችን ጨምሮ በየደረጃው ለሚገኙ የመንግስት ሹሞች ተፈቅዶ የነበረው የደሞዝ ጭማሪ እንዲቀር ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡

 

ለሹሞቹ ከ2 እስከ 5 በመቶ የደሞዝ ጭማሪ ለማድረግ ታስቦ ነበር ተብሏል፡፡

 

ርዕሰ ከተማዋ ናይሮቢን ጨምሮ በተለያዩ ታላላቅ ከተሞች ከትናንት በስቲያ አደባባይ የወጡ የተቃውሞ ሰልፈኞች ከፀጥታ ሀይሎች ጋር ተጋጭተዋል፡፡

 

ከሳምንት በፊት ተቃውሞ ባስከተለው ግጭት የ40 ያህል ሰዎች ሕይወት ማለፉ እየተነገረ ነው፡፡


 

አዲሱ የደቡብ አፍሪካ የብሔራዊ አንድነት መንግስት የካቢኔ አባሎች ቃለ መሐላ በመፈፀም ሀላፊነታቸው ተረከቡ፡፡

 

በደቡብ አፍሪካ ጥምር መንግስት ሲመሰረት ከ30 አመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው፡፡

 

በአዲሱ ካቢኔ ውስጥ 32 ሚኒስትሮች መካተታቸው ታውቋል፡፡

 

20ዎቹ ሚኒስትሮች እስከ ቅርቡ ገዢ የፖለቲካ ማህበር ከነበረው የአፍሪካ ብሔራዊ ኮንግረስ (ANC) ወገን እንደሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

ነጮች የሚልቁበት ዴሞክራቲክ አሊያንስ ደግሞ 6 የሚኒስትርነት ቦታዎችን አግኝቷል፡፡

 

ሌሎች ስምንት የሚኒስትርነት ሹመቶች ደግሞ ለተቀሩት 5 የጥምር መንግስቱ አባል የፖለቲካ ማህበራት እንደተደለደሉ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡

 

 

የሴራሊዮኑ ፕሬዘዳንት ጁሊየስ ማዳ ባዮ በአገሪቱ ያለ እድሜ ጋብቻን የሚያነውር እና የሚከላክለው ህግ ስራ ላይ እንዲውል ፊርማቸውን አኖሩበት፡፡

 

በሴራሊዮን ሲሶ ያህሉ ሴቶች እድሜያቸው 18 አመት ሳይደርስ እንደሚያጋቡ አሶሼትድ ፕሬስ አስታውሷል፡፡

 

እንደውም 800 ሺህ ያህል ሴቶች እድሜያቸው 15 አመት ሳይሞላ የተዳሩበት አገር እንደሆነች ተጠቅሷል፡፡

 

አዲሱን ህግ በመተላለፍ አዳጊ ሴቶችን የሚያገቡ እስከ 15 አመት በሚደርስ እስራት ይቀጣሉ ተብሏል፡፡

 

ከዚህም በላይ እስከ 4 ሺህ ዶላር የሚደርስ ምንዛሪ ግምት ያለው የገንዘብ መቀጫም ይቆነደዳሉ ተብሏል በነፍስ ወከፍ፡፡

 

የህጉ ስራ ላይ መዋል በሴቶች መብት ተከራካሪዎች ዘንድ እንደ ከፍተኛ ድል መቆጠሩ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

 

በአሜሪካ የዴሞክቲክ የፖለቲካ ማህበሩ ቱባ ቱባዎች በፕሬዘዳንት ጆ ባይደን በፕሬዘዳንታዊ እጩነት መቀጠል ጉዳይ እየተከፋፈሉ ነው ተባለ፡፡

 

ከፊሉ በእጩነታቸው ይቀጥሉ ሲሉ ፤ ሌሎቹ ደግሞ በሌላ እጩ ይተኩ እያሉ መሆኑን ዘ ዋሽንግተን ታይምስ ፅፏል፡፡

 

በአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአሪዞናው እንደራሴ ራውል ግሪጃልቫ ፕሬዘዳንት ባይደን በቃ እጩነታቸውን ይተውት ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ቀደም ሲልም የቴክሳሱ እንደራሴ ሎይድ ዶጌት ተመሳሳይ ጥያቄ ማቅረባቸው በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

ባይደን ባለፈው ሳምንት ከቀድሞ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ባደረጉት የቴሌቪዥን የምርጫ ክርክር ነበራቸው የተባለው ድክመት ሰሞኑን ታላቅ መነጋገሪያ ወጥቶታል፡፡

 

ጉዳዩ ባይደን የሚገኙበትን የዴሞክራቲክ የፖለቲካ ማህበሩን አባሎች ሳይቀር በውዝግብ እያመሳቸው ነው ተብሏል፡፡

 

እንደ እቅዱ ከሆነ ትራምፕ እና ባይደን በመጪው መስከረም ወርም 2ኛ የቴሌቪዥን ክርክራቸውን ያደርጋሉ፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

Comments


bottom of page