top of page

ሰኔ 6፣ 2016  - የ27 ሀገራት ስብስብ የሆነው የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ምርጫ ከቀናት በፊት ተካሂዷል።

በዚህም ምርጫ ‘’ቀኝ ዘመም’’ የሆኑ የፖለቲካ ፓርቲዎች ድል እንደቀናቸው በሰፊው ተነግሯል።

 

የህብረቱ የፓርላማ አባላት በአባል አገራት በሚገኙ የፖለቲካ ፓርቲዎች ወይም በግል ተወዳድረው ይመረጣሉ።

 

በአውሮፓ ደረጃ ራሳቸውን በፖለቲካ ፓርቲ አደራጅተው እየተወዳደሩ መቀመጫ የሚይዙም አሉ።

 

የክርስትያን ዴሞክራቶች ፓርቲ* ስብስብ የሆነው እና በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል (EPP) በሚል የሚታወቀው ፓርቲ አንዱ ነው።

 

S & D የተሰኘው ‘’የሶሻል ዴሞክራቶች ስብስብ’’ እንዲሁም ብሄርተኞች ይበዙበታል የሚባለው ሌላው የፖለቲካ ማህበር በተመሳሳይ ይጠቀሳሉ።

 

የአውሮፓ ህብረት አጠቃላይ የፓርላማ አባላት ብዛት አሁን ላይ 720 ሲሆን ጀርመን 96 ፤ ፈረንሳይ 81 እና ጣሊያን 76  ተወካዮችን በማስመረጥ ቀዳሚዎቹ ናቸው።

 

ብዙ ህዝብ ያለው አገር ብዙ ተወካዮችን ያስመርጣል በሚለው የህብረቱ ህግ መሰረት ነው አገራቱ ቀዳሚ የሆኑት።

 

ከ720 በላይ የፓርላማ አባላት ለሚሰየሙበት ምርጫ ከ370 ሚሊየን በላይ ህዝብ ድምጽ ለመስጠት እንደተመዘገበ ቀደም ብለው የወጡ መረጃዎች አሳይተዋል።

 

የህብረቱ በአጠቃላይ የህዝብ ብዛት 450 ሚሊየን ነው።

 

የዘንድሮው የአውሮፓ ህብረት የፓርላማ አባላት ምርጫ ከፍተኛ የህዝብ ተሳትፎ የታየበት እንደሆነ ተነግሯል።

 

መራጮች በዚህን ያህል ብዛት ወጥተው ድምጽ ለመስጠት መፈለጋቸው በህብረቱ ለውጥ እንዲመጣ መፈለጋቸውን ያሳያል ተብሏል።

 

በኦስትሪያ ፤ ፈረንሳይ ፤ ጀርመን ፤ ግሪክ ፤ ፖላንድ ፤ ስፔይን እና ሃንጋሪ ቀኝ ዘመም የፖለቲካ ፓርቲዎች አሸንፈዋል።

 

እነዚህ ፓርቲዎች ከህብረቱ አጠቃላይ ፓርላማ እስከ 32 በመቶውን ሊይዙ ይችላሉ ነው የሚባለው።

 

የአባል አገራትን ፍላጎት በአውሮፓ ደረጃ ለማስጠበቅ ይሰራሉ የሚባሉት እነዚህ ተመራጮች ቀዳሚ ተግባራቸው የህብረቱን ኮሚሽነር መምረጥ እንደሚሆን ተነግሯል።

 

የክርስትያን ዴሞክራቶች ፓርቲ ስብስብ የሆነው እና በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል (EPP) በሚል የሚታወቀው ፓርቲ ሚስ ቮንዴር ሌየርን በኮሚሽነርነት የማስመረጥ ፍላጎት እንዳለው ተጠቅሷል።

 

የፓርቲው ፍላጎት እውን የሚሆነው ግን ሌሎች ቀኝ ዘመም ፓርቲዎች በሚያሳዩት ትብብር ይሆናል ተብሏል።

 

ፓርቲዎቹ የሴትዮዋን እጩነት ለመደገፍ  ቁልፍ ፤ ቁልፍ  በሚባሉ ጉዳዮች ላይ ከ(EPP) ጋር ተደራድረው ስምምነት ላይ መድረስ እንደሚኖርባቸው ነው የተጠቀሰው።

 

ይህ ደግሞ አጠቃላይ የአውሮፓ ህብረት አቋም በራሱ ቀኝ ዘመም እንዲሆን ሊያደርግ ይችላል እየተባለ ነው።

 

ለምሳሌም በስደተኞች ፤ ፀጥታ እና የአየር ንብረት ለውጥ ዙሪያ።

 

በሩስያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ከአሁኑ የተለየ አቋም በህብረቱ ዘንድ ሊወሰድ እንደሚችል ተገምቷል።

 

  ይሄ የቀኝ ዘመሞቹ የበላይነት በፓርላማው ሙሉ ለሙሉ ከሰፈነ ነው።

 

አለበሊዚያ ግን ህብረቱ የሽኩቻ መድረክ ይሆናል ሲል አሶሼትድ ፕሬስ ጽፏል።

 

ይህ ደግሞ ሌላ የተወሳሰበ ችግር በአውሮፓ ህብረት ላይ እንደሚያስከትል የተለያዩ የፖለቲካ ሰዎች መናገር ጀምረዋል።

 

 ሁለቱ የአለም ታላላቅ ጦርነቶች አውሮፓ ውስጥ እንደተቀሰቀሱ የሚያስታውሱት እነዚህ የፖለቲካ ሰዎች የአይሁዶች ጭፈጨፋም በዚያው በአውሮፓ መፈጸሙን ይጠቅሳሉ።

 

የአውሮፓ አገራት ተሰባስበው ህብረት የፈጠሩትም እንዲህ አይነቱን አውዳሚ ክስተት በአንድነት ለመከላከል ነው ሲሉ ያክላሉ።

 

በጊዜው አይን እና ናጫ የነበሩ አገራት አንዱ ለሌላው ድንበሩን ክፍት ማድረጉን በንግድም መተሳሰራቸውን ጨምረው ይጠቃቅሳሉ።

 

አንዳንዶቹ የጋራ ደህንነትን ለማረጋገጥ በሚል ሉአላዊነታውን ጭምር ለድርድር አቅርበዋልም ብለዋል።

 

የህብረቱ የጋራ መገበያያ ገንዘብ የሆነው ዩሮም አውሮፓን በአለም አቀፍ ደረጃ ተወዳዳሪ እንዳደረጋት ያነሳሉ።

 

የተደመረው የኢኮኖሚ አቅማቸው ማዕቀብ ሲጥሉ ሁሉ የሚያሳምሙ እንዲሆኑ አድርጓቸዋልም ብለዋል።

 

የዚህ ማዕቀብ ሠለባ የሆኑት የሩስያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን የህብረቱን መከፋፈል የመፈለጋቸው መነሻም ይኸው እንደሆነ ተናግረዋል።

 

በሌላ በኩል የህብረቱ የዴሞክራሲ እሴቶች እና የዴሞክራሲ ተቋማት በአንዳንድ አባል አገራት ችግር እየገጠማቸው እንደሚገኝ የሚናገሩ አሉ።

 

በጀርመን ፤ ስሎቫኪያ እና ዴንማርክ የፖለቲካ ብጥብጥ አዝማሚያዎች መታየታቸውን ፤ በሃንጋሪ በነፃ ሚዲያ ላይ እቀባ ለመጣል መሞከሩን በመጥቀስም ሃሳባቸውን አፍታተውታል።

 

ከሞላ ጎደል በሁሉም የህብረቱ አባል አገራት ይታያል የተባለው ያልተገባ የስደተኞች አያያዝ ጉዳይም እንዲሁ ተነስቷል።

 

የአውሮፓ ህብረት የሩስያ ዩክሬን ጦርነት መቀስቀሱን ተከትሎ ያልተቋረጠ ድጋፉ ለዩክሬን ሆኖ ቆይቷል።

 

አምስት አባል አገራቱ ከሩስያ ጋር የሚዋሰኑት ህብረቱ ነገሩን እንደ ቀላል ስጋት አልተመለከተውም ።

 

በዚህም ምክንያት በቢሊየን ዶላሮች የሚገመት የገንዘብ እና የጦር መሳሪያ ድጋፍ ለዩክሬን አድርጓል።

 

በሩስያ ባለስልጣናት ፤ ኩባንያዎች እና የነዳጅ ዘርፍ ላይም አይነተ ብዙ ማዕቀቦችን ጥሏል።

 

ለዩክሬን በሚሰጥ በዚህ አይነቱ ድጋፍ እና በሩስያ ላይ በሚደረጉ ጫናዎች ላይ ፍፁማዊ ለውጥ በቅርብ ጊዜ ይኖራል ተብሎ አይገመትም።

 

በሂደት ግን የዩክሬን ጉዳይ በፓርላማው በቀላሉ ስምምነት የሚደረስበት ላይሆን ይችላል ተብሏል።

 

ይህንኑ የአውሮፓ ህብረት ፓርላማ አባላት ምርጫ ተከትሎ የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአገራቸውን ፓርላማ በትነዋል።

 

 

ማክሮን ፓርላማውን የበተኑት በእንግሊዝኛው ምህጻረ ቃል NR የተሰኘው እና በወይዘሮ ማሪን ሊፐ የሚመራው ቀኝ ዘመም ፓርቲ ካሸነፈ በኋላ ነው።   

 

ለህብረቱ የፓርላማ አባላት በፈረንሳይ በተደረገው ምርጫ የማሪን ሊፐ ፓርቲ ከ31 በመቶ በላይ ድምጽ ማግኘቱ ተነግሯል።



ንጋቱ ረጋሣ ያዘጋጀውን በምህረት ስዩም

 

Comments


bottom of page