top of page

ሰኔ 7፣ 2016 ሳፋሪኮም “ሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል

ሳፋሪኮም ከገበያ ኩባንያ ጋር፣ እንዲሁም የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ (JICA) ድጋፍ ታክሎበት “ሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ” የተሰኘ ፕሮግራም ይፋ አድርጓል፡፡


ይህም ፕሮግራም የኢትዮጵያን የሥራ ፈጠራ ሥነ ምህዳር በእጅጉ የሚያሳድግ ነው ተብሏል፡፡


ፕሮግራሙ የመረጃ መረብን በመጠቀም የሥራ ዕድልን የሚፈጥር መሆኑ የተነገረለት ሲሆን በዓይነቱ የመጀመሪያ የሆነና ቀጣዩን የቴክኖሎጂ ባለሙያዎች፣ ሥራ ፈጣሪዎች እንዲሁም የዲጅታሉ ዓለም መሪዎችን አቅም ለማሳደግ ያለመ እንደሆነ ተነግሯል።


የተለየ አሠራርን ይዞ መጥቷል የተባለው ፕላትፎርም እስከ 2024 እ.ኤ.አ ማብቂያ ድረስ፣ ለ10 ሺህ ልዩ ልዩ ክህሎት ያላቸው ኢትዮጵያውያን ሠራተኞች አጠቃላይ የአቅም ግንባታ እንዲሁም የሥራ ጉዟቸውን ማሳደጊያ ዕድሎችን የሚያቀርብ ነው መባሉን ሰምተናል ።


"የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ “ለመጪው ዲጂታል ዘመን የኢትዮጵያንን ሕይወት ዝግጁ ማድረግ” የሚለውን የሳፋሪኮም ተልዕኮ የሚወክል ነው” ሲሉ የሳፋሪኮም ኢትዮጵያ ዋና የስትራቴጂ ኦፊሰር ማሳሂሮ ሚያሺታ ተናግረዋል።


“መጪው ጊዜ ይዟቸው ለመጣቸው ዕድሎች ያለውን ተደራሽነት ለሁሉም በማደላደል፣ አዳዲስ ነገሮችን የሚፈጥር አዲስ ትውልድ የሚነሣበትን መሠረት በመጣል ላይ እንገኛለን ያሉት ማሳሮሂ ሚያሺታ አገልግሎቱ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ (AI) የሚጠቀመውንና እንደ ሁኔታው ተስማሚ በሆነ መልኩ ሥራ ላይ ሊውል የሚችለውን ሶፍትዌርን እንደ አገልግሎት የሚያቀርበውን (SaaS) ፕላትፎርም በመጠቀም፣ የላቀ የቴክኖሎጂ ችሎታን አንጥሮ በማውጣት እንደየ ድርጅቱ ፍላጎት ተስማሚ መፍትሔን የሚያቀርብ ነው ብለዋል።

አገልግሎቱን ለበርካታ ስመ ጥር የዓለም ግዙፍ የቴክኖሎጂ ኩባንያዎችና የፎርቹን 500 ኩባንያዎች ተስማሚ ሥነ ምህዳር መፍጠሩንም ተነግሯል።


ሳፋሪኮም፣ ገበያ ኩባንያ እና የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ አብረው ሲሠሩ ይህ የመጀመሪያቸው አለመሆኑ የተነገረ ሲሆን በመጋቢት ወር 2016 ዓ.ም እነዚሁ ተቋማት ጋር 50 የተመረጡ ችሎታ ያላቸውን ሠራተኞች መልምለው በጋራ “ሳፋሪኮም አካዳሚን” መመስረታቸው ተነግሯል።


ሳፋሪኮም አካዳሚ የስድስት ወር ፈጣን የሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ሥልጠና ፕሮግራም ሲሆን፣ የሞባይል፣ የ “ባክ ኢንድ” (Back-end) እንዲሁም “ዴቭ ኦፕስ” (DevOps) ምህንድስና ላይ፣ እንዲሁም የጀማሪ ደረጃ “ባክ ኢንድ” ሶፍትዌር ዴቨሎፕመንት ላይ ክህሎት የሚሰጥ ነው ተብሏል።


በተጨማሪም፣ በ2024 እ.ኤ.አ ገበያ ኩባንያ በኦንላይን የቴክኖሎጂ ትምህርት ዓለም አቀፍ መሪ ከሆነው ፕሉራልሳይት (Pluralsight) ጋር ተፈራርሟል።


የሳፋሪኮም ታለንት ክላውድ ዲጂታል ክህሎቶችን ለማሳደግ ይዞ የተነሣቸው ዓላማዎች በመላው ኢትዮጵያ በተቻለ መጠን ለሁሉም ተደራሽ መሆናቸውን ለማረጋገጥ ጥረት በማድረግ ላይ እንደሚገኝ የተነገረለት ሲሆን እስካሁን በአገሪቱ በሚገኙ ክልሎች ውስጥ ከሚገኙ ዋና ዋና ዩኒቨርሲቲዎች ጋር አጋርነትን ፈጥሯል ተብሏል።


ከዚህ በተጨማሪ፣ የጃፓን ዓለም አቀፍ ትብብር ኤጀንሲ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ ተጎጂ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ለማገዝ በማሰብ፣ የፕሮግራሙ ተሳታፊነትን ወጪ መደጎሚያ የሚሆን ቀላል የማይባል ገንዘብ መድቧል ተብሏል።


ታለንት ክላውዱ ከዛሬ ጀምሮ ምዝገባ ለመቀበል ክፍት የሚደረግ ሲሆን፣ ለመላው የኢትዮጵያ ትውልድ ዲጂታል አቅምን መገንቢያ ዕድል የሚያቀርብ ይሆናል መባሉን አሰምተናል።

የቴክኖሎጂ ኩባንያ የሆነው ሳፋሪኮም፣ ዘርፈ ብዙ አገልግሎትችንና መፍትሔዎችን የሚያቀርብ ሲሆን የሞባይል የድምፅ ጥሪ፣ የመልእክት፣ የፈጣን ኢንተርኔት፣ የፋይናንስ (“M-PESA” በተሰኘ የብራንድ መጠሪያ) ጨምሮ ሌሎች አገልግሎቶችን ይሰጣል።

Comments


bottom of page