በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ መከልከሉን አልሰማንም ያሉ ሰዎች ገዝተው እያመጡ መሆኑን የትራንስፖርት እና ሎጀስቲክስ ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ ተናገሩ፡፡
መስሪያ ቤታቸውም በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎች ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ በተባለው አግባብ ብቻ እንደሚሰራ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
ማንኛውም የቤት አውቶሞቢል የኤሌክትሪክ ካልሆነ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገባ መንግስት ቀደም ሲል ውሳኔ ማሳለፉን ሚኒስትሩ ዓለሙ አንስተዋል፡፡
ሚኒስትሩ ይህን ያሉት በዛሬው እለት በህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት የመስሪያ ቤታቸውን የ6 ወር እቅድ አፈፃፀም ለከተማ፣ መሰረተ ልማትና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ባቀረቡበት ወቅት ነው፡፡
ለተሽከርካሪዎች ነዳጅ የሚወጣው የውጭ ምንዛሬ ከፍተኛ መሆኑ፣ በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ በስፋት መመረቱ እና ከነዳጅ ጋር ሲነፃፀር ርካሽ መሆኑ እንዲሁም ኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ደጋፊ መሆኗ በነዳጅ የሚሰሩ የቤት አውቶሞቢሎችን ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገቡ ክልከላ ለመጣል ምክንያት ከሆኑት መካከል ይገኙበታል ሲሉ ሚኒስትሩ አስረድተዋል፡፡
በኤሌክትሪክ የሚሰሩ ተሽከርካሪዎች በአለም ላይ በስፋት እየተመረቱ መሆኑንን የጠቀሱት ሚኒስትሩ ዓለሙ ስሜ በሀገር ውስጥም ለሀይል መሙያ (ቻርጅ ማድረጊያ) ቦታዎችን በቶሎ ማዳረስ ይቻላል ብለዋል፡፡
ማንኛውም የግል መገልገያ አውቶሞቢል ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባት የሚቻለው የኤሌክትሪክ ከሆነ ብቻ መሆኑንን ያሰመሩበት ሚኒስትር ዓለሙ ሰሞኑንን ይህን አልሰማንም በሚል በነዳጅ የሚሰሩ አውቶሞቢሎችን ገዝተው ያመጡ መኖራቸውን አስድተዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments