የሳምንቱን መጨረሻ ጠብቀው በየአካባቢው የሚዘረጉት የገበያ ማዕከላቱ በአብዛኛው የአትክልትና ፍራፍሬ ምርቶች፤ አልፎ አልፎም የፋብሪካ ውጤቶች የሚሸጡበት ነው፡፡
ነጋዴዎቹ የሱቅ ኪራይም ይሁን ግብር የማይከፍሉበት፤ በምትኩ በሚጧቸው እቃዎች ላይ ከመደበኛ ገበያው ከ15 እስከ 20 በመቶ የዋጋ ቅናሽ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
በተጨማሪም ይህንን ስራ በባለቤትነት የሚቆጣጠረው የከተማዋ ንግድ ቢሮ በሚተምነው የእቃዎች የዋጋ ዝርዝር መሰረት የመሸጥ ግዴታም አለባቸው፡፡
ለመሆኑ እነዚህ 207 የሚደርሱት ገበያዎች በዚህ መንገድ እሸጡ ነው ወይ? የሚለውን ሸማቾችን ጠይቀናል፡፡
ያነጋገርናቸው ሸማቾች እንደሚሉት ገበያዎቹ በተለይ በእረፍት ቀናት በየአካባቢው መኖራቸው ጥሩ ሆኖ ሳለ፤የአንዳንዶቹ እቃዎች ዋጋ ከመደበኛ ገበያው ብዙም ለውጥ የለውም፤ነጋዴዎቹ በንግድ ቢሮ በሚለጠፈው ዋጋ የሚሸጡንል ተቆጣጣሪዎች ሲኖሩ ነው ብለውናል፡፡
በእነዚህ ገበያዎች መሸመት ከፍ ያለ የዋጋ ልዩነት አለው ቢባል እንኳን ይህ የሚሆነው በብዛት ሲገዛ ነው ይሁንና እኛ አነስ ባለ ገቢ የምንተዳደር ሰዎች አቅም ስለማኖረን በብዛት ልንገዛ አንችልም የሚል ሃሳብም አንስተዋል፡፡
የዋጋ ንረቱ እየጨመረ በመጣበት በዚህ ጊዜ ዝቅተኛ ገቢ ያለውን ለመደገፍ ከሆነ የታሰበው በቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች የሚቀርቡ ምርቶች ዋጋቸው አሁን ካለውም ሊቀንስ ይገባል የሚሉት ሸማቾቹ በየገበያዎቹ በሚለጠፈው የዋጋ ዝርዝር መሰረት መሸጥ አለመሸጡን መንግስት አበርትቶ ቁጥጥር እንዲያደርግበት ጠይቀዋል፡፡
ሸገር ራዲዮም በተባሉት የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ባደረገው ቅኝት በተለይ የፍራፍሬ ምርቶች ከ15 እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንዳላቸው ተመልክቷል፡፡
ለአብነትም ሙዝ በመደበኛው ገበያ60 ብር ሲሸጥ በቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ግን 40ብር ይሸጣል፤አቮካዶ በመደበኛው ገበያ 60 ብር በእነዚህ ገበያዎች ግን ከ30 እስከ 40 ብር ይሸጣል፤ሌሎቹም ተመሳሳይ የዋጋ ቅናሽ አላቸው፡፡
ይሁንና የአትክልት ምርት በሆኑት ከሽንኩርትና ቲማቲም በስተቀር ድንች፣ካሮት፣ ቀይስር፣ቃሪያ የመሳሰሉት ምርቶች ዋጋቸው በኪሎ ያላቸው ቅናሽ ከ5 እስከ10 ብር መሆኑን በቅኝቱ ተመልክቷል፡፡
ጉዳዩን አስመልክቶ ስራውን በበላነት የሚቆጣጠረውን የከተማዋ ንግድ ቢሮ የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች ከመደበኛ ገበያዎች ስለምን የዋጋ ልዩነታቸው ቅሬታ አስነሳ ስንል ጠይቀናል፡፡
በቢሮው የገበያ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሰማ ጀማል በየገበያዎቹ የምንለጥፋቸው የዋጋ ተመኖች እስከ 20 በመቶ ቅናሽ እንዳላቸው አረጋግጠን ነው፤ነገር ግን አንዳንድ ምርቶች በየቀኑ ዋጋቸው ሊጨምረና ሊቀንስ ችላል፤እኛ ዝርዝሩን ካወጣን በኋላ በመደበኛ ገበያዎች የምርቶች ዋጋ ሊቀንስ ይችላልብለዋል፡፡
በተጨማሪም በሸማቹ የተነሳው በዋጋ ዝርዝሩ መሰረት አለመሸጥ እንዳለ አምነው፤የሚወሰደውን እርጃ ሲያስረዱ ካሉት 207 የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች 14ቱ በዚህ ተግባር ውስጥ ገብተው በመገኘታቸው በቅርቡ አግደናቸዋል ብለዋል፡፡
የቅዳሜና እሁድ ገበያዎች መዘርጋት ያለባቸው ከቅዳሜ ጠዋት እስከ እሁድ አመሻሽ ብቻ እንደሆነ ያነሱት ሃላፊው ከአርብ ከሰዓት ጀምሮ ድንኳን የሚዘረጉ ነጋዴዎች በሰጠናቸው ዋጋ የማሸጡ ናቸው፤እንዲህ የሚያደርጉትን እየከለከልናቸው ነው አስረድተዋል፡፡
እንዲህ አይነት ችግሮች ሲገጥሙ በ8588 የነፃ የስልክ መስመር ደውላችሁ የት አካባቢ እንዳለና የድንኳን ቁጥሩን ጭምር ብትነግሩን ፈጠን ያለ እርምጃ እንወስዳለን ተብላችዋል፡፡
Comments