ቤት ለቤት የሚቀርቡ የድጎማ ምርቶች ዋጋ በመንግስት ድጎማ እየተደረገባቸው በተለይ ዝቅተኛ ገቢ ያላቸውን የማህበረሰብ ክፍሎች ለመደገፍ በሚል በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ በኩል የሚቀርቡ ስኳር፣ ዘይትና የዳቦ ዱቄት ምርቶች እንዳሉ ይታወቃል፡፡
በሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በኩል የሚቀርቡት እነዚህ ምርቶች ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በ4 ክፍለ ከተሞች (በአዲስ ከተማ፣ ልደታ፣ ንፋስ ስልክ ላፍቶና ኮልፌ ቀራኒዮ) ሸማች ህብረት ስራ ማህበራት በየወረዳው ያከፋፍሉት የነበረውን በማስቀረት ቢሮው ማኪባ ከተባለ ድርጅት ጋር በመሆን ቤት ለቤት እያደረሰ ይገኛል፡፡
በዚህ መንገድ በ4ቱ ክፍለ ከተሞች 320,000 ሰዎች የድጎማ ምርቶች ባሉበት እየቀረበላቸው ነው ተብሏል፡፡
በእነዚህ አካባቢዎች ምርቶቹ በምን ያህል ዋጋ እየቀረቡ እንደሆነና አገልግሎቱ ቀድሞ ከነበረው ምን ለውጥ እንዳለው ሸማቾችን ጠይቀናል፡፡
ሸማቾቹ እንደሚሉት ድጎማ ተደርጎበታል ተብሎ ሰፈራችን ድረስ የሚመጣው ስኳር በኪሎ 110 ብር ነው፤ በተጨማሪም የዳቦ ዱቄትም በኪሎ 100 ብር እየገዛን ነው፤ሌላውም ዘይት፣ በቆሎ ዱቄት፣ ፓስታና መኮረኒም ዋጋቸው በየሱቁ ከምንገዛው ብዙም የተለየ አይደለም ብለውናል፡፡
በመንግስት እንደመቅረቡ ዋጋው መቀነስ ነበረበት ከመደበኛ ሱቆች ያለው የዋጋ ልዩነት ከ10 እስከ 20 ብር ነው ይላሉ፤በየቤታችን መቅረቡ ምንም እንኳን ለረጅም ሰዓት ተሰልፈን ከመግዛት ቢገላግለንም ቢያንስ በየወሩ እንኳን ቢመጡንን መልካም ነበር ብለውናል፡፡
ምርቶቹን ቤት ለቤት በማድረስ ስራ ላይ የተሰማራው ማኪባ ጠቅላላ ንግድ በበኩሉ እነዚህ በሸማቾች የቀረቡ ጥያቆዎች ትክክል ናቸው፤ ጊዜቸውን ጠብቀው አይመጡም የተባለው ትክክል ነው እናስተካክላለን፣ ከዚህ በኋላ በየ15 ቀኑ ምርቶቹን ለማድረስ እየሰራሁ ነው ብሏል፡፡
ዋጋን በተመለከተም ዋጋ የሚተምንልን የከተማዋ የንግድ ቢሮ ነው፤ ዋጋ ይቀንስልን የሚል ተደጋጋሚ ጥያቄ እየቀረበልን ስለሆነ ይህ ችግር እንዲፈታ ለቢሮው ጥያቄያችንን አቅርበናል፤የድጎማ ምርቶቹ ዋጋ ከመደበኛው ጋር የተቀራረበው የ15 በመቶ ቫት ጭማሪ በመንግስት ስለተደረገባቸው ነው ያሉን የማኪባ ጠቅላላ ንግድ ዋና ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ አዋሽ መሃመድ ናቸው፡፡
የድጎማ ምርቶቹ አቅራቢ በሆነው በአዲስ አበባ ንግድ ቢሮ የገበያ መረጃና ጥናት ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ሙሰማ ጀማል የቤት ለቤት ሽያጩ ከዚህ ቀደም የነበሩትን ረጃጅም ሰልፎችን አስቀርቷል፤ዋጋውም ቢሆን ተመጣጣን ነው፤ ይህንን ስራ በሁሉም ክፍለ ከተሞች የማዳረስ ፍላጎት አለን ስራ ላይ ካለው ድርጅት በተጨማሪ ሌሎች ሁለት ድርጅቶች ወደ ስራው ለመግባት ፕሮፖዛላቸውን አቅርበው እየታየላቸው ነው ብለውናል፡፡
ምርቶቹን ቤት ለቤት የማድረስ ስራ እየሰራ ያለው ማኪባ ጠቅላላ ንግድ የማህበረሰቡ ድላጎት እየጨመረ በመምጣቱ ከ4ቱ በተጨማሪ በቅርቡ በ2 ክፍለ ከተሞች ማለትም በጉለሌና በአቃቂ ክፍለ ከተሞች የደምበኞች ምዝገባ ላይ መሆኑን አቶ አዋሽ ነግረውናል፡፡
ድርጅቱ ስለ ሚሰጠው አገልግሎት መረጃ ማግኘት የሚፈልጉ ደምበኞቹን የሚያስተናግድበት የ6009 የጥሪ ማዕከል ጥሪዎችን የማስተናገድ አቅም ካለው የደምበኛ መጠን ጋር የሚመጣጠን ባለመሆኑ ብዙዎችን ማስተናገድ አልቻልኩም ነገር ግን አገልግሎቱን ለማስፋት እየሰራ መሆኑን ከሃላፊው ሰምተናል፡፡
ሙሉ ዘገባውን ያድምጡ
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Commenti