top of page

ታህሳስ 1፣2016 –  የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Dec 11, 2023
  • 2 min read

 

ግብፃውያን ቀጣይ ፕሬዘዳንታቸውን ለመምረጥ ከትናንት አንስቶ ድምፅ እየሰጡ ነው፡፡

 

ድምፅ አሰጣጡ እስከ ነገ ድረስ እንደሚከናወን ኒው ዴይሊ ፅፏል፡፡

 

ፕሬዘዳንት አብዱልፈታህ አል ሲሲን ለመፎካከር ሶስት እጩዎች መቅረባቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

አልሲሲን ለመፎካከር የቀረቡት ሶስት እጩዎች እምብዛም የማይታወቁ ናቸው ተብሏል፡፡

 

አንዳንድ ወገኖች መንግስት ሁነኞቹን እጩዎች አዋክቦ አባሯቸዋል የሚል ወቀሳ እያቀረቡ ነው፡፡

 

በምርጫው አብዱልፈታህ አል ሲሲ ማሸነፋቸው ሳይታለም የተፈታ ነው እየተባለ ነው፡፡

 


 

የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ዲፕሎማቶች አገሩን ለቅቀው እንዲወጡ አዘዛቸው፡፡

 

15 የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ ዲፕሎማቶች ሱዳንን ለቀው እንዲወጡ መታዘዛቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

ትዕዛዙ ለኢሚሬትስ ኤምባሲ ጉዳይ ፈፃሚዋ ተነግሯቸዋል ተብሏል፡፡

 

የኢሚሬትስ ዲፕሎማቶች ሱዳንን ለቅቀው እንዲወጡ የታዘዘበት ምክንያት አልተጠቀሰም፡፡

 

የተባበሩት አረብ ኢሚሬትስ እንደ ቻድ እና ማዕከላዊ አፍሪካ ባሉ አገሮች በኩል RSF ለተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል የጦር መሳሪያ በማቀበል ስሟ እንደሚነሳ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡

 

የሱዳን መንግስት ጦር እና  RSF በጦርነት ላይ መሆናቸው ይታወቃል፡፡

 

ጦርነቱ ያለ ሁነኛ መፍትሄ ወደ 8ኛ ወሩ ተቃርቧል፡፡

 

 

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤኒያሚን ኔታንያሁ አሸባሪዎች ያሏቸውን የሀማስ ታጣቂዎች መሳሪያቸውን አስቀምጠው እጅ እንዲሰጡ አስጠነቀቁ፡፡

 

ኔታንያሁ የጋዛው ጦርነት አሁን ያለበት ደረጃ የሐማስ ፍፃሜ መጀመሪያ ነው ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ሐማሶችን ከማለቅ እጃችሁን ብትሰጡ ይሻላችኋል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ሐማስ በበኩሉ እስራኤል በእስር ቤቷ የሚገኙ ፍልስጤማውያን እስረኞችን ካልፈታች አንድም ታጋች በሕይወት አታገኝም ሲል ዝቷል፡፡

 

ሐማስ ከ2 ወራት በፊት በደቡባዊ እስራኤል ድንገት ደራሽ ጥቃት ባደረሰበት ወቅት ከ240 የማያንሱ ታጋቾችን ወደ ጋዛ ማምጣቱ ይነገራል፡፡

 

በእስረኞች ልውውጥ ከፊሉ ቢለቁም አሁንም ከ100 የማያንሱ ታጋቾች በእጁ ላይ እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡

 

 

የፍልስጤም አስተዳደር ፕሬዘዳንት ማሐሙድ አባስ እስራኤል በጋዛ ፍልስጤማውያን ላይ ታደርሰዋለች ባሉት እልቂት አሜሪካም ተጠያቂ ነች አሉ፡፡

 

አባስ በጋዛው እልቂት አሜሪካም ተጠያቂ ነች ያሉት በጋዛ ዘላቂ የተኩስ አቁም እንዲደረግ ለፀጥታው ምክር ቤት የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ውድቅ ማድረጓን ተከትሎ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

ብሪታንያም በወቅቱ ድምፅ ተአቅቦ አድርጋለች፡፡

 

ውሳኔው በ13 የምክር ቤቱ አባላት ቢደገፍም አሜሪካ ድምፅን በድምፅ የመሻር መብቷን ተጠቅማ ፉርሽ አድርጋዋለች፡፡

 

አሜሪካ በዚህ እርምጃዋ ከየአቅጣጫው እየተነቀፈች ነው ተብሏል፡፡

 

ከአሜሪካ በተጨማሪ ሩሲያ ፣ ብሪታንያ ፣ ፈረንሳይ፣ እና ቻይና በፀጥታው ምክር ቤት ድምፅን በድምፅ የመሻር መብት ያላቸው አገሮች ናቸው፡፡

 

 

የኔነህ ከበደ

 

የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page