top of page

ታህሳስ 11፣ 2015- የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ማህበር በ2014 በጀት ዓመት ከታክስ በኋላ 223.5 ሚሊየን ትርፍ ማግኘቱን ተናገረ


የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን ማህበር በ2014 በጀት ዓመት ከታክስ በኋላ 223.5 ሚሊየን ትርፍ ማግኘቱን ተናገረ።


ትርፉ ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ጋር ሲነፃፀር የ289 ሚሊዮን ብር ወይም የ14.6 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።


በዚህም ከጠቅላላ መድን ዘርፍ 193.3 ሚሊዮን ብር እና የሕይወት መድን ዘርፍ ድርሻ ደግሞ 30.2 ሚሊዮን ብር መሆኑ ተነግሯል።


የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማህበር ከመንግስት የልማት ድርጅቶች እና ከግሉ ዘርፍ የተወጣጡ 7 ባንኮች፣ 17 መድን ሰጪ ኩባንያዎች፣ 93 ግለሰቦች እና 1 የሰራተኛ ማህበርን የያዘ ነው።


ኩባንያው በጀት ዓመቱ 1.36 ቢሊየን ብር የአረቦን ገቢ ማግኘቱን ዛሬ የባለአክስዮኖች ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ከቀረበው ሪፖርት ላይ ተመልክተናል።


ገቢው ከቀዳሚው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲመሳከር የ19 በመቶ ብልጫ አሳይቷል።

ከአረቦን ገቢው አብዛኛው የተገኘው ከጠቅላላ መድን ሲሆን ይህም 1.6 ቢሊዮን ብር ነው።


ከህይወት መድን የተገኘው ደግሞ 60.8 ሚሊዮን ብር መሆኑን ሰምተናል።


በጊዜ ማዕቀፉ 190 ሚሊዮን ብር ከኢንቨስትመንት ማግኘቱንም ኩባንያው አስረድቷል።


ኩባንያው በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 392.9 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ መፈፀሙን ተናግሯል።


የካሳ ክፍያው ከእቅዱ የ54.4 ሚሊዮን ብር ወይንም የ14 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል።


ለካሳ ክፍያው መጨመር ኩባንያው ለዋልያ ኢንዱስትሪ የባህር ላይ ጉዞ የተከፈተው ካሳ፣ በሶማሌ ክልል ለአየር ንብረት እንዲሁም በተሽከርካሪና በቦንድ ዘርፍ የተከፈሉ የካሳ ክፍያዎች በዋና ምክንያትነት ቀርበዋል።


የኢትዮጵያ ጠለፋ መድን አክሲዮን ማህበር አጠቃላይ ካፒታሉ 1.7 ቢሊዮን ብር፣ ሀብቱ ደግሞ 3.1 ቢሊዮን ብር መድረሱን በሪፖርቱ ተጠቅሷል።


በ2014 በጀት ዓመት የኢትዮጵያ መድን ኢንዱስትሪ 16.7 ቢሊዮን ብር የአረቦ ገቢ ማግኘቱን ሰምተናል።


በአገሪቱ ውስጥ ካሉት 1 የመንግስት እና 17 የግል መድን ኩባንያዎች አጠቃላይ ሀብት 40.8 ቢሊዮን ብር ደርሶለቸዋል።


ንጋቱ ሙሉ


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page