top of page

ታህሳስ 18፣2017 - በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሾች የሚያደርሱት ንክሻ የእብድ ውሻ በሽታን ወደ ሰዎች ያስተላልፋሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡

በአዲስ አበባ ባለቤት አልባ ውሾች ቁጥር በጣም ጨምሮ ከ300 ሺህ በላይ እንደደረሰ ይገመታል፤ እነዚህ ውሾች የሚያደርሱት ንክሻ የእብድ ውሻ በሽታን ወደ ሰዎች ያስተላልፋሉ የሚል ስጋት ፈጥሯል፡፡


ከእነዚህ አካባቢዎች አንዱ አስኮ አካባቢ የሚገኘው ሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም ነው፡፡ 5,000 ነዋሪዎች ባሉበት በዚህ አካባቢ እየተፈጠረ ያለው የባለቤት አልባ ውሾች ንክሻ ነዋሪውን ስጋት ውስጥ ከትቶታል ተብሏል፡፡


ችግሩ የተፈጠረው በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ አስኮ ብርጭቆ ወይም ሚኪሊላንድ እየተባለ በሚጠራው ኮንዶሚኒየም አካባቢ ነው፡፡


በአካባቢው በሚርመሰመሱ ባለቤት የሌላቸው ውሾች ልጆቻችንና አቅመ ደካሞች እየተነከሱ ነው፤ በወር 5 እና 6 ሰዎች ይነከሳሉ፤ በዚህም ምክንያት ለመውጣትም ይሁን ለመግባት ተቸግረናል የአስኮ ሚኪሊ ላንድ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎች ነግረውናል፡፡


ውሾቹ ከእለት እለት ቁጥራቸው እየጨመረ መጥቷል፤ የሚመለከተው አካል መፍትሄ ይስጠን ሲሉ ቅሬታቸውን አቅርበዋል፡፡


ስለ ጉዳዩ ጠየቅነው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር አርሶ አደርና ከተማ ግብርና ልማት ኮሚሽን፤ በሚኪሊላንድ ኮንዶሚኒየም የተፈጠረው ተደጋጋሚ የውሻ ንክሻን በተመለከተ ወደ ኮሚሽኑ የመጣ ቅሬታ እንደሌለ ነግሮናል፡፡

በኮሚሽኑ የእንሰሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ሃኪም ዶክተር ታደሰ ከበደ (ዶ/ር) በከተማዋ እየተከወነ ባለው የኮሪደር ልማት የሚነሱና ወደ ሚሰጣቸው ኮንደሚኒየም ቤቶች የሚገቡ ሰዎች የነበሯቸውን ውሾች ባሉበት ጥለዋቸው ስለሚሄዱ ይህ ጉዳይ ባለቤት የሌላቸውን ውሾች ቁጥር ጨምሮታል፡፡


ይሁንና ውሾቹ በነዋሪው ጤና ላይ ጉዳት ጉዳት እንዳያደርሱ ባለቤት ያላቸውንም የሌላቸው ውሾች በሙሉ እየከተቡ መሆኑን ዶ/ር ታደሰ ከበደ ነግረውናል፡፡


እስካሁን በ6 ክፍለ ከተሞች ክትባቱን መስጠታቸውን የሚናገሩት ባለሙያው በተቀሩት ክፍለ ከተሞች በዘመቻ የመከተብ ስራ ይሰራል ብለውናል፡፡


መፍትሄ ይሰጠን ሲሉ የጠየቁንን የሚኪሊ ላንድ ኮንዶሚኒየም ነዋሪዎችን በተመለከተ፤ ባለሙያው በሰጡን ምላሽ ቅሬታ አቅራቢዎቹ የሚገኙበት የኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ክትባቱ ካልደረሳቸው መካከል ነው፤ በጣም በቅርቡ መጥተን ውሾቹን እንከትባለን ብለውናል፡፡


ከዚህ ቀደም ለማህበረሰቡ ስጋት የሆኑ ውሾችን ሙያዊ መንገድ በመግደል ማስወገድ ይቻል እንደነበር ያስታወሱት ባለሙያው የሚወገዱበት መርዝ ለስነ ምህዳሩ አደገኛ በመሆኑ ወደ ሃገር ቤት እንዳይገባ እንደተከለከለ ጠቅሰዋል፡፡


ስለሆነም አሁን ውሾቹን በሙሉ በመከተብና ጤናቸውን እየጠበቅን ነው፤ ሴቶቹን በማምከን እንዳይዋለዱ እያደረግን ነው የሚሉት ዶ/ር ታደሰ ይሁንና በየትኛውም አጋጣሚ በውሾች የመነከስ አደጋ ከደረሰ ወዲያው የተነከሰውን ቦታ በሳሙናና በውሃ በመታጠብ ወደ ህክምና መሄድ ያስፈልጋል፡፡


ንክሻው ከወገብ በላይ ከሆነ የበለጠ አደገኛ ስለሚሆን በቶሎ ወደ ህክምና በመሄድ የሚሰጠውን ክትባት መውሰድ ያስፈልጋል ሲሉ በኮሚሽኑ የእንሰሳት በሽታ መከላከልና መቆጣጠር ከፍተኛ ሃኪም የሆኑት ዶክተር ታደሰ ከበደ መክረዋል፡፡



ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


Comments


bottom of page