top of page

ታህሳስ 21፣2017  - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

ግብፅ የስዌዝ የባህር መተላለፊያ ቦይ ማስፋፊዋን አስሞከረች፡፡

 

ማስፋፊያው የ10 ኪሎ ሜትር ርዝማኔ እንዳለው ማላይ ሜይል ፅፏል፡፡

 

ቅዳሜ የተሞከረው ማስፋፊያው ሁለት መርከቦች ማሳለፉ ታውቋል፡፡

ማስፋፊያው የስዌዝ ቦይን መርከቦችን የማስተላለፍ ቅልጥፍና እንደሚያሳድገው ታምኖበታል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት የየመን ሁቲዎች በቀይ ባህር ተላላፊ መርከቦች ላይ በሚሰነዝሩት ጥቃት የተነሳ ዘንድሮ የስዌዝ ቦይ ገቢ በ70 በመቶ እንደቀነሰ ተጠቅሷል፡፡

 

የስዌዝ ቦይ ከሜዴትሬኒያን ወደ ቀይ ባህር ማቋረጫ በመሆኑ ይታወቃል፡፡

 

 

ቻዳውያን የምክር ቤታዊ ተወካዮቻቸውን ለመምረጥ ትናንት ድምፅ ሲሰጡ ዋሉ፡፡

 

ትናንት በቻድ ለምርጫ ድምፅ የተሰጠው የፓርላማ ፣ ግዛታዊ እና አካባቢያዊ ተወካዮችን ለመምረጥ እንደሆነ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡

 

ምርጫው የተካሄደው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበራት ደጋፊዎቻቸው ድምፅ ከመስጠት እንዲታቀቡ ጥሪ ባቀረቡበት አጋጣሚ መሆኑ ታውቋል፡፡

 

የዋነኛው የተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር መሪ ምርጫውን የተቃወምነው ውጤቱ ከመካሄዱ አስቀድሞ ስለሚታወቅ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

ገዢው የፖለቲካ ጥምረት ከምርጫው አስቀድሞ ለማሸነፍ ተሰናድቻለሁ ማለቱ ተጠቅሷል፡፡

 

ቀደም ሲል ተከናውኖ በነበረው ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ ማርሻል ማኅማት ኢድሪስ ዴቢ አሸናፊ መደረጋቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

በደቡብ ኮሪያ ሙአን አለም አቀፍ ኤርፖርት ባጋጠመ የአውሮፕላን መከስከስ አደጋ የ179 ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡

 

ሁለት የአውሮፕላኑ ሰራኞች በሕይወት ተርፈው ወደ ሆስፒታል እንደተወሰዱ ቢቢሲ ፅፏል፡፡

 

አውሮፕላኑ ከመከስከሱ አስቀድሞ ክንፉ በአሞሮች ሳይመታ አልቀረም ተብሏል፡፡

 

ያም ሆኖ ስለ አደጋው ትክክለኛውን ምክንያት ለመናገር ጊዜው ገና እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡

 

ለክፉ ዕጣ የተዳረገው አውሮፕላን የአውሮፕላን አደጋው የገጠመው ከታይላንድ መጥቶ በሙአን ኤርፖርት በማረፍ ላይ በነበረበት ወቅት ነው፡፡፡

 

አደጋው በደቡብ ኮሪያ ከፍተኛ ሐዘን ፈጥሯል፡፡

 

የኤርፖርቱ የማረፊያ እና የማኮብኮቢያ ሜዳ ለቀናት ዝግ ሆኖ እንደሚሰነብት ታውቋል፡፡

 

የደቡብ ኮሪያ መንግስት ከትናንት አንስቶ የሳምንት ብሔራዊ ሐዘን ማወጁ ተሰምቷል፡፡

 

 

 የኔነህ ከበደ

 

 

 

Comments


bottom of page