የጋና መንግስት የሁሉም የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ወደ አገሪቱ ያለ ቪዛ እንዲገቡ ፈቀደ፡፡
የአፍሪካ ሀገሮች ዜጎች ወደ ጋና ያለ ቪዛ እንዲገቡ መፈቀዱ የሀገሪቱን የንግድ እና የቱሪዝም ዘርፎች በእጅጉ እንደሚያሳድገው የታመነበት መሆኑን አፍሪካ ኒውስ ፅፏል፡፡
የ26 የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ወደ ጋና ያለምንም ቪዛ እንዲገቡ ተፈቅዶላቸዋል፡፡
የሌሎች 25 የአፍሪካ አገሮች ደግሞ ጋና እንደደረሱ ቪዛ ማግኘት ይችላሉ ተብሏል፡፡
የ2 የአፍሪካ አገሮች ዜጎች ብቻ የቪዛ ሰነዶችን እንደሚጠየቁ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ሩዋንዳ፣ ጋምቢያ፣ ሲሼልስ እና ቤኒንም የጋናን መሰል መላን እንደሚከተሉ መረጃው አስታውሷል፡፡
ጣሊያን ኢራን ውስጥ የታሰረችባት ጋዜጠኛ በአፋጣኝ እንድትለቀቅ ጠየቀች፡፡
ሲሶሊያ ሳለ የተባለችው ጣሊያናዊት በኢራን የፀጥታ ሀይሎች ከታሰረች 2 ሳምንታት ገደማ እንደሆናት ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
በዚህ ጉዳይ የጣሊያን የውጭ ጉዳይ ሹሞች የኢራኑን አምባሳደር በማስጠራት ጋዜጠኛዋ በአፋጣኝ እንድትለቀቅ መጠየቃቸው ተሰምቷል፡፡
እንደሚባለው ጋዜጠኛዋ የታሰረችው ለብቻዋ ነው፡፡
መሰረታዊ ቁሳቁሶች እንዳይደርሷት እና ሰውም እንዳይጠይቃት መደረጉ ተጠቅሷል፡፡
የኢራን ሹሞች ጋዜጠኛዋን ያሰርናት የአገራችንን ህግ ተላልፋ ተገኝታለች ብለው ነው፡፡
ዝርዝሩን ግን እንዳላፍታቱት በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የፍልስጤም አስተዳደር ባለስልጣናት መሰረቱን በዌስት ባንክ አድርጎ የሚሰራውን የአልጀዚራን የአረብኛ ቋንቋ ክፍል አገዱት፡፡
የፍልስጤም ባለስልጣናት የጣቢያውን የዌስት ባንክ የአረብ ክፍል ያገዱት የተዛቡ መረጃዎችን ያሰራጫል ብለው እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በዚህ ላይ የዌስት ባንክ ፍልስጤማውያንን ለአመፅ የሚያነሳሱ ፕሪግራሞችን እያቀረበ ነው ሲሉ ከስሰውታል፡፡
በቅርቡ የፍልስጤም የፀጥታ ሀይሎች በጄኒን ፅንፈኛ ባሏቸው ታጣቂዎች ላይ የወሰዱትን እርምጃ በተመለከተ አልጀዚራ ያቀረበው ዘገባ ሹሞቹን አስቆጥቷቸዋል ተብሏል፡፡
ጣቢያው በእስራኤል በእንግሊዘኛ እና በአረቢኛ ቋንቋዎች አሰናድቶ ያቀርባቸው የነበሩ ዝግጅቶች ከተከለከሉ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡
በአሜሪካ ካሊፎርኒያ አንዲት ትንሽ የመጓጓዣ አውሮፕላን ከአንድ ፋብሪካ ሕንፃ ጋር በመላተሟ የሁለት ሰዎች ሕይወት አለፈ፡፡፡
በአደጋው 18 ሌሎች ሰዎች ደግሞ የተለያየ ደረጃ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቢቢሲ ፅፏል፡፡
በአደጋው አካላዊ ጉዳት ከገጠማቸው መካከል 10ሩ በሆስፒታል ሕክምና እየተደረገላቸው ነው፡፡
ስምንቱ የህክምና እርዳታ አግኝተው መሸኘታቸው ታውቋል፡፡
በአደጋው ሕይወታቸው ያለፈው በአውሮፕላኗ ተሳፍረው የነበሩ ናቸው ተብሏል፡፡
አውሮፕላኗ ከሕንፃው ጋር በተላተመችበት ወቅት ቃጠሎ ተቀስቅሶ ነበር፡፡
በአደጋው ወቅት ፖሊስ በህንፃው ውስጥ የነበሩ በሙሉ ለቅቀው እንዲወጡ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡
በአካባቢው መሰል አደጋ ሲደርስ በ2 ወር ጊዜ 2ኛው ነው ተብሏል፡፡
አውሮፕላኗ በምን ምክንያት ከሕንፃው ጋር የመላተም አደጋ እንደገጠማት ለጊዜው ምክንያቱ አለመታወቁ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ ሀገራቸው ለ130,000 ዩክሬናውያን ስደተኞች የምትሰጠውን የገንዘብ እርዳታ ልታቋርጥ እንደምትችል በብርቱ አስጠነቀቁ፡፡
የፊኮ ማስጠንቀቂያ የተሰማው የዩክሬይን መንግስት በግዛቱ በኩል ወደ ስሎቫኪያ የሚያልፈውን የሩሲያን የጋዝ አቅርቦት ካቋረጠ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ዩክሬይን ወደ አውሮፓ አገሮች ሲላክ የቆየውን የሩሲያን የጋዝ አቅርቦት ያቋረጠችው ከትናንት በስቲያ አንስቶ ነው፡፡
ስሎቫኪያ የጋዝ አቅርቦቷ እንዳይቋረጥ ዩክሬይንን በብርቱ ስታስጠነቅቅ ሰንብታለች፡፡
የስሎቫኪያው ጠቅላይ ሚኒስትር ሮበርት ፊኮ የዩክሬይንን እርምጃ አሻጥር ሲሉ ጠርተውታል፡፡
እንደ ማልዶቫ ያሉ አገሮችም የጋዝ አቅርቦቱ በመቋረጡ ችግር ላይ መውደቃቸው ተሰምቷል፡፡
ስሎቫኪያም ከሩሲያ የጋዝ አቅርቦት ተጠቃሚነቷ ባለፈ እሷም የማስተላለፊያ የአገልግሎት ክፍያ ስታገኝ መቆየቷን መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5rs
Comments