ባለፋት 5 ዓመታት በትራፊክ አደጋ መከላከል ላይ የተከወኑ ስራዎች ውጤት ቢኖራቸውም ኢትዮጵያ አሁንም ጥቂት ተሽከርካሪ ይዘው በርካታ አደጋ ከሚደርስባቸው ሀገራት ውስጥ ነች ተባለ።
የትራንስፖርት እና ሎጅስቲክስ ሚኒስቴር የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከኃይማኖት አባቶች፣ ከሀገር ሽማግሌዎች ፣ ከአሽከርካሪ ማሰልጠኛ ባለቤቶች እና ከተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት ጋር ዛሬ በአዳማ ገልማ አባገዳ አዳራሽ ምክክር አካሂዷል።
የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ የተከወኑ ስራዎች ለምን ለውጣቸው አልታየም ለሚለው በርካታ ምክንያቶች ተጠቅሰዋል።
የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነትና ብቃት ማነስ 68 በመቶ የተሽከርካሪ የቴክኒክ ችግር 14 በመቶ ለችግሩ ድርሻ አላቸው ተብሏል።
ኢትዮጵያ 1.4 ሚሊየን ያህል የተሽከርካሪ ቁጥር ቢኖራትም በአደጋ ብዛት ግን ከአለም 19ኛ ደረጃ ላይ እንደሆነች የመንገድ ደህንነትና መድዕን ፈንድ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ጀማል አባሶ ተናግረዋል።
በትራፊክ አደጋ የሚደርሰው ጉዳት በሀገሪቱ ላይ ከፍተኛ ቀውስ እየፈጠረ በመሆኑ በምክክሩ ላይ የተገኙት ጉዳዩ በቀጥታ የሚመለከታቸው የአሽከርካሪ ማሰልጠኛ እና የተሽከርካሪ ምርመራ ተቋማት እንዲሁም ተጽዕኖ ፈጣሪ የማህረሰብ ክፍሎች ለችግሩ መፍትኤ ላይ ሊሳተፋ ይገባል ብለዋል አቶ ጀማል።
በተለይ ለአደጋው ዋና መንስኤ ተብለው ለተጠቀሱት ችግሮች ፍቃድ ሰጪውም ይሁን አሰልጣኝ ተቋማት ትልቅ ኃላፊነት አለባቸው ሲሉ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስትሩ አለሙ ስሜ ተናግረዋል።
ችግሩ አንድ ቦታ ላይ ካልተገታ እና በጊዜ መፍትሔ ካልተሰጠው ሁሉም ላይ ተጽዕኖ ማሳረፋ አይቀርም ብለዋል ሚኒስትሩ።
በኢትዮጵያ በ2015 ዓ.ም 3 ሺህ 577 ወይም በቀን 10 ሰዎች በትራፊክ አደጋ ህይወታቸውን አጥተዋል ተብሏል።
ከ 10,000 በላይ የሚሆኑት ደግሞ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ሰምተናል።
ምህረት ስዩም
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
コメント