top of page

ነሐሴ 19፣2015 - ብዙ የውሃ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው እየተጠናቀቁ አይደለም ተባለ


የውጪ ምንዛሪ እጥረት፣ የጥሬ እቃዎች ዋጋ መናር፣ የፀጥታ ችግርና ሌሎችም፤ የተያዙ የውሃ ፕሮጀክቶች በታቀደላቸው ጊዜ እንዳይጠናቀቁ አድርገዋል ተባለ፡፡


በተለይም የኤል.ሲ ፈቃድ መዘግየት ብዙ ፕሮጀክቶች በጊዜያቸው እንዳይጠናቀቁ ማድረጉ ተሰምቷል፡፡


በእነዚሁ ውስብስብ ችግሮች ምክንያት አንዳንድ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ከተያዘላቸው ጊዜ ብዙ ዘግይተውም አሁንም ስራቸው ከ50 እና ከ60 በመቶ መሻገር አልቻለም ተብሏል፡፡


የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር በስሩ ያሉ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት የስራ አፈፃፀም ግምገማን ዛሬ በሳይንስ ሙዚየም ማካሄድ ጀምሯል፡፡


ከዚህ ቀደም ባልተለመደ ሁኔታ በስራ ውስጥ ያሉ የግል እና የመንግስት የስራ ተቋራጭ ፣አማካሪ ድርጅቶችና ተቆጣጣሪ ተቋማት በእጃቸው ያሉ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ሪፖርታቸውን እንዲያቀርቡ በተደረገበት ጉባኤ ላይ ድርጅቶቹ ያለባቸውን ችግርና ኮንትራት ወስደው የተረከቧቸው ፕሮጀክቶች የደረሱበትን ደረጃ በተመለከተ ማብራሪያ እያቀረቡ ነው፡፡


ብሉ ማትሪክስ በተባለ አማካሪ ተቋም የቀረበ ማብራሪያ በኦሮሚያ፣ በደቡብ እና በሌሎችም ክልሎች እየተሰሩ ያሉ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች እና ያሉበትን ደረጃ አሳይቷል፡፡


የቡኢ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን በተመለከተ የቀረበው ማብራሪያ እንደሚያስረዳው ፕሮጀክቱ መጠናቀቅ ካለበት የ12 ወር ኮንትራት ጊዜ አልፎ 604 ቀን ሆኖታል፡፡


አሁንም ግን ኮንትራቱ የሚገኘው 21 በመቶ የግንባታ ደረጃ ላይ ነው ተብሏል፡፡


ከ289 ሚሊየን ብር በላይ እንዲሁም ከ12.8 ሚሊየን ዩሮ በላይ ወጪ ይሆንበታል ተብሎ ኮንትራት የተገባለት የመተሐራ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የተያዘለት ጊዜ ቢያልፍም አሁንም የፕሮጀክቱ ስራ 51 በመቶ ላይ ነው ተብሏል፡፡


የቱሉ ሚልኪ፣ የአዳባ፣ የወራቤ፣ የሆለታ፣ የፊቼ እና ሌሎችም የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ማብራሪያ ቀርቧል፡፡


ብዙዎቹ አማካሪዎችና ኮንትራክተሮች ስራዎቹን ለማጠናቀቅ የሚያስፈልጉ የፓምፕና የሌሎችም እቃዎች ግዢን ለመፈፀም የውጭ ምንዛሬ ማግኘት ፈተና እንደሆነባቸው ተነግሯል፡፡


በሀገር ውስጥ የጥሬ እቃ በበቂ ደረጃ በገበያ አለመገኘት፣ ዋጋውም የናረ መሆን እና ሌሎችም፤ ድርጅቶቹ እየገጠሙን ነው ካሏቸው ችግሮች ውስጥ ናቸው፡፡


በኦሮሚያ እና በሌሎችም አካባቢዎች ያሉ አንዳንድ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቶች ደግሞ በፀጥታ ችግር ምክንያት ስራቸው እየተስተጓጎለ ነው ተብሏል፡፡


በቅርቡ ስራው ተጠናቆ ርክክብ ከተደረገባቸው ፕሮጀክቶች መካከል የደብረ ፅጌ ከተማ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት በምሳሌነት ተነስቷል፡፡


በ2015 በጀት ዓመት 6.2 ሚሊየን ሕዝብ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ቢደረግም ዘርፉ የተለያዩ ችግሮች የሚነሱበት ስለሆነ በስራ ውስጥ ያሉት ሁሉ ተገናኝተው በግልፅ መነጋገር እንዲችሉ በማሰብ የስራ እቅድ ግምገማው መዘጋጀቱን የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶ/ር ሀብታሙ ኢተፋ ተናግረዋል፡፡


በ2015 በጀት ዓመት 6.5 ሚሊየን ህዝብ የመጠጥ ውሃ እንዲያገኝ ቢታቀድም መሳካት የቻለው 6.2 ሚሊየን ነው ብለዋል ሚኒስትሩ፡፡


በዚህ ዘርፍ በመንግስት የተመደበው እና ከለጋሾችም የተገኘውን ጨምሮ በአጠቃላይ ለዘርፉ በበጀት ዓመቱ 8.3 ቢሊየን ብር መገኘቱን የተናገሩት ዶ/ር ሀብታሙ ከዚህ ገንዘብ ውስጥ በበጀት ዓመቱ 7.5 ቢሊየን ብሩን ተጠቅመናል ብለዋል፡፡


በመጠጥ ውሃ ዘርፍ ብዙ ፕሮጀክቶች እየተጠናቀቁ ቢሆንም አሁንም ከፍላጎቱ ጋር መጣጣም ስላልቻለ በየአካባቢው ከፍተኛ ቅሬታ እየተነሳ ነው ብለዋል፡፡


ዛሬ የተጀመረው የውሃና እና ኢነርጂ ሚኒስቴር የ2015 በጀት አመት የስራ አፈፃፀም ግምገማ ለ3 ቀናት ይቆያል ተብሏል፡፡



ቴዎድሮስ ወርቁ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz

Comments


bottom of page