top of page

ነሐሴ 22፣2016 - ወርቅ አምራች ኩባንያዎች ከወርቅ ሽያጭ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለ3 ወራት አንዲጠቀሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቀደ

ወርቅ አምራች ኩባንያዎች ከወርቅ ሽያጭ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለ3 ወራት አንዲጠቀሙ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ፈቀደ፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የወርቅ ግብይት ዋጋን አስመልክቶ የተሻሻለ የአሰራር መመሪያ አውጥቷል፡፡


የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በውጭ ምንዛሪ ግብይት ላይ ያደረገው ስማሻሻያ ለወርቅ አቅራቢዎች ዘላቂ ማበረታቻ እንደሚፈጥር በመታመኑ እና የወርቅ አቅርቦትን በዘላቂነት ማሻሻል አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱየተሻሻለ መመሪያ ለማውጣት ማስፈለጉን አስረድቷል፡፡


ከባህላዊ የወርቅ ምርት ዘርፍ አገሪቱ ማግኘት የሚገባትን የውጭ ምንዛሪ በዘላቂነት እንዲገኝ ለማስቻልና እንዲሁም አቅራቢዎችን ሊያበረታታ የሚችል አሰራር መተግበር አስፈላጊ ሆኖ ተገኝቷልም ብሏል፡፡


የወርቅ ዋጋን አስመልክቶ ከሐምሌ 24 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ በዋለው አሰራር መሰረት የወርቅ መግዣ ዋጋ በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ድረ-ገፅ  ላይ በየዕለቱ በሚገለጸው የውጭ ምንዛሪ መሸጫ ተመን ላይ ተመስርቶ የሚወሰን ሆኗል፡፡


ወርቅ አቅራቢ ማህበራትን/ግለሰብ ነጋዴዎችን ለማበረታታት ታስቦ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ባስቀመጠው አሠራር መሠረት አቅራቢዎች ላቀረቡት ወርቅ 95 በመቶ ክፍያ በቅድሚያ በመውሰድ እና ቀሪውን 5 በመቶ የዋጋ መጠበቂያ በማድረግ ወርቁን ለግዢ ማዕከላት ካስረከቡበት ቀን ጀምሮ በ30 ተከታታይ ቀናት ከተመዘገበው ዋጋ መርጠው በሚያቀረቡት መሰረት ክፍያ ያገኛሉ ሲል ባንኩ ዛሬ ባወጣው መግለጫ አስረድቷል፡፡


30ኛው ቀን የበዓላት ወይም የሳምንቱ የእረፍት ቀን ከሆነ እስከሚቀጥለው የስራ ቀን ድረስ ዋጋ መምረጥ የሚችሉ ሆኖ ከ30 ቀናት በኋላ ደንበኛው ካልቀረበ በ31ኛው ቀን በሚውለው የወርቅ ዋጋ ባንኩ ይገዛል ተብሏል፡፡


ትላልቅ አምራቾች/ኩባንያዎች ከወርቅ ሽያጭ ከሚያገኙት ገቢ 50 በመቶ በውጭ ምንዛሪ ለራሳቸው መጠቀሚያ እንዲሁም ቀሪውን 50 በመቶ  በእለታዊ የውጪ ምንዛሪ ተመን እየታሰበ ክፍያ ያገኛሉ ሲል በባንኩ ዋና ገዢ ማሞ አስመለዓለም ምህረቱ ተፈርሞ የወጣው መመሪያ ያስረዳል፡፡


በኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የውጭ ምንዛሪ መመሪያ መሰረት በዚህ መልክ የሚገኘውን የውጭ ምንዛሪ ይዘው መጠቀም የሚቻለው ለአንድ ወር ጊዜ ብቻ ቢሆንም፤ ወርቅ አምራች ኩባንያዎችን ማበረታታት እንዲቻል ከወርቁ ሽያጭ የሚያገኙትን የውጭ ምንዛሪ ለ3 ወራት ይዘው የሚጠቀሙ ይሆናል ተብሏል፡፡


በዚህ መልክ የሚቀርበው ወርቅ በብሔራዊ ባንክ እና በወርቅ አምራች ኩባንያዎች መካከል በሚደረገው ውል መሰረት በባንኩ በኩል ወደ ውጭ እየተጓጓዘ ይነጠራል ተብሏል፡፡


በአንድ ጊዜ ከ250.01 ግራም ጀምሮ እስከ 25 ኪ.ግራም ወርቅ ለሚያቀርቡ ወርቅ አቅራቢዎች በባንኩ የውስጥ አሰራር መመሪያ መሰረት ወጪያቸውን እንዲሸፍኑ ለማስቻል ማበረታቻ እየተደረገ ባንኩ ግዢ እፈጽማለሁ ብሏል፡፡


በአንድ ጊዜ ከ25.01 ኪ.ግራም በላይ ከአቅራቢዎች በመሰብሰብ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ለሚያቀርቡ አቅራቢዎች በባንኩ የውስጥ አሰራር መመሪያ መሰረት ወጪያቸውን ሸፍነው ገቢ የሚያገኙበት ከፍ ያለ ማበረታቻ እየተደረገ ግዢ ይፈጸማል ተብሏል፡፡


ይህ ማሻሻያ ከዛሬ ነሐሴ 21 ቀን 2016 ዓ.ም ጀምሮ ተፈጻሚ ይሆናል ሲሉ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ዋና ገዢው ማሞ አስመለዓለም ምህረቱ አስረድተዋል፡፡

Comments


bottom of page