በተመራጩ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ለአገሪቱ ጠቅላይ ዐቃቤ ህግነት ታጭተው የነበሩት ማት ጋኤትዝ ሀላፊነቱን መረከብ ይቅርብኝ አሉ፡፡
ስማቸው ከእጩዎች ዝርዝር እንዲወጣላቸው መጠየቃቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ማት ጋኤትስ ነቀፋ፣ ተቃውሞ እና ትችት በርትቶባቸው ከሰነበቱት የወደፊቱ የትራምፕ አስተዳደር እጩ ተሿሚዎች መካከል አንዱ እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡
ዝርዝሩ ለአደባባይ ባይበቃም ማት ጋኤትዝ በወሲባዊ ቅሌት እና በሥነ ምግባር ብልሹነት ጉዳያቸው በአሜሪካ ኮንግረስ ኮሚቴ ሲመረመር ቆይቷል ተብሏል፡፡
የጠቅላይ ዐቃቤ ሕግነቱን ሀላፊነት ከመረከባቸው አስቀድሞ የምርመራ ግኝቱ ይፋ እንዲደረግ ጎትጓቶች በርትተውባቸው ነበር፡፡
ማት ጋኤትስ ለጠቅላይ ዐቃቤ ህግነት ከታጩ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከአሜሪካ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባልነታቸው እንደለቀቁ በመረጃው ለትውስታ ተጠቅሷል፡፡
ተመራጩ ፕሬዘዳንት በማት ጋኤትስ ምትክ ፓም ቦንዲ የተባሉ ወይዘሮን ለአቃቤ ህግነት ማጨታቸው ተሰምቷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ለዩክሬይን ግዛት ተሻጋሪ የጦር መሳሪያዎችን በማስታጠቅ ሩሲያን ለጥቃት የሚያጋልጡ አገሮችን ከመምታት እንደማይመለሱ አስጠነቀቁ፡፡
ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ዩክሬይን አሜሪካ ስሪቶቹን አገር አቋራጭ ሚሳየሎች ተጠቅማ ሩሲያን እንድትመታ የፈቀዱት በቅርቡ ነው፡፡
ዩክሬይንም ምእራብ ስሪቶቹን ሚሳየሎች ወደ ሩሲያ መተኮስ ጀምራለች፡፡
ፑቲን በዚህ ዓይነቱ ሁኔታ የዩክሬይን አስታጣቂ አገሮችን ለመምታት እንገደዳለን ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት ማስጠንቀቂያ መረር ፣ ከረር ያለ እና ቀጥተኛ እንደነበር TRT ዎርልድ አስታውሷል፡፡
በአሁኑ ወቅት ጦርነቱ ከዩክሬይን እና ከሩሲያ ጦርነትነቱ አልፎ አለም አቀፋዊ ባህሪን እየተላበሰ መምጣቱን መረጃው አስታውሷል፡፡
ፑቲን በማስጠንቀቂያቸው አትጠራጠሩ ለእያንዳንዱ ነገር ምላሽ አለው ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡
ሩሲያ በዩክሬይን ላይ በሙከራ ላይ የሚገኝ ዘመን አፈራሽ መካከለኛ ርቀት ተወንጫፊ ሚሳየል መተኮሷን ፕሬዘዳንት ፑቲን አረጋግጠዋል፡፡
በፓኪስታን ሰሜናዊ ክፍል ተከታትለው በሚያልፉ ተሽከርካሪዎች በተከፈተ ተኩስ በጥቂቱ 38 ሰዎች ተገደሉ ተባለ፡፡
ጥቃቱ የተፈፀመው ፓኪስታን ከአፍጋኒስታን ጋር በምትዋሰንበት ኩራም በተባለ ስፍራ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የጥቃት ፈፃሚዎቹ ማንነት አልተለየም ተብሏል፡፡
በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈው በተጨማሪ 11 ሰዎች ደግሞ አካላዊ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተጠቅሷል፡፡
ከተገደሉት እና ጉዳት ከደረሰባቸው መካከል ህፃናት እና ሴቶችም እንደሚገኙበት ተጠቅሷል፡፡
የሰሜናዊ ምዕራብ ፓኪስታን የተለያዩ ፅንፈኛ ቡድኖች መናኸሪያ መሆኑ ይነገራል፡፡
ከወር በፊትም በዚያው ቀጠና በህዝብ ማጓጓዣ ላይ በተፈፀመ ጥቃት የ15 ሰዎች ህይወት ማለፉን መረጃ አስታውሷል፡፡
በኢራቅ የኢራን አጋሮች የሆኑ በሰው አልባ በራሪ አካላት(ድሮኖችን) ተጠቅመን በሰሜናዊ እስራኤል በሚገኝ የጦር ተቋም ላይ ጥቃት ፈፅመናል አሉ፡፡
ታጣቂዎቹ በእስራኤል የጦር ተቋም ላይ ጥቃት ያደረስነው ለጋዛ ፍልስጤማውያን ድጋፍ ነው ማለታቸውን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን ካላቆመች ጥቃታችን ይቀጥላል ብለዋል፡፡
በሰሜናዊ የእስራኤል ክፍል ላይ ተሰነዘረ በተባለው የድሮን ጥቃት ስለደረሰው ጥቃት የተጠቀሰ ነገር የለም፡፡
በዚህ ጥቃት ጉዳይ ከእስራኤል ጦር በኩል አስተያየት አልተሰጠም፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://t.ly/9uH-g
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments