በሳውዲ አረቢያ በልምምድ ላይ የነበረ የጦር አውሮፕላን መከስከሱ ተሰማ፡፡
የተከሰከሰው ቶርኔዶ የተሰኘ የጦር አውሮፕላን እንደሆነ የሳውዲ የመከላከያ ሹሞች መናገራቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
የአውሮፕላኑ አብራሪዎች መትረፋቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
አውሮፕላኑ የተከሰከሰው በድሃህራን በሚገኘው የአየር ሀይል ሰፈር አቅራቢያ እንደሆነ ታውቋል፡፡
አውሮፕላኑ በተከሰከሰበት ወቅት በምድር ላይ በአንድም ሰው ላይ ጉዳት አልደረሰም ተብሏል፡፡
የመከስከስ አደጋው እንዴት እንዳጋጠመ አልታወቀም፡፡
ምርመራው መቀጠሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ከሀላፊነት የታገዱት የሊቢያዋ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ናጅላ ማንጉሽ አገር ጥለው መውጣታቸው ተሰማ፡፡
ከሀላፊነት የታገዱት የትሪፖሊው አስተዳደር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አገር ጥለው የወጡት ባለፈው ሳምንት በጣሊያን ሮም ከእስራኤሉ አቻቸው ኤሊ ኮኸን ጋር ሚስጥራዊ ንግግር አድርገዋል መባሉ በአገሪቱ ከፍተኛ ቁጣን መቀስቀሱን ተከትሎ ነው፡፡
ማንጉሽ ወደ ቱርክ መኮብለላቸውን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ሚስጥራዊው ንግግር ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነትን በመመስረት ላይ ያተኮረ እንደነበር የእስራኤል የውጭ ጉዳይ ሹሞች ተናግረዋል፡፡
በሊቢያ ከግማሽ ምዕተ አመት በፊት ከእስራኤል ጋር ማንኛውም ዓይነት ግንኙነት መመስረት የሚከላክል ህግ ስራ ላይ መዋሉን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ሊቢያውያን በአብዛኛው የፍልስጤማውያን የነፃነት ትግል ደጋፊዎች መሆናቸው ይነገራል፡፡
በየኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ… https://bit.ly/33KMCqz
Comments