top of page

የካቲት 11 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Feb 18
  • 2 min read

የሱዳን ወታደራዊ መንግስት መሪ ጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን በውጭ ተቀምጠው ስልጣን ለሚቋምጡ የአገሪቱ ፖለቲከኞች በጭራሽ ቦታ የለንም አሉ፡፡


የአል ቡርሃን ነቀፋ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሐምዶክ በሚመራው እና በምህፃሩ ታካዱም ተብሎ በሚጠራው የሲቪል ማህበራት ጥምረት ላይ ያነጣጠረ እንደሆነ አናዶሉ ፅፏል፡፡


አል ቡርሃን በውጭ ሆኖ ጥምረቱ ለሚፈጥርብን ጫና በጭራሽ አንበረከክም ብለዋል፡፡

ጥምረቱ ለሱዳን ልባዊ ተቆርቋሪነት ካለው ወደ አገር ቤት ገብቶ የRSF ሀይሎችን ለመዋጋት መሰለፍ ይኖርበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡


ታካዱም በአፍሪካ ህብረት እና በምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት /ማህበር/ ኢጋድ በኩል በሱዳን መንግስት ላይ ጫና እያሳደረ ነው ይባላል፡፡


ያም ሆኖ አልቡርሃን ይሄ ዓይነቱ ሙከራ በእኛ ዘንድ ተቀባይነት የለውም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡



የአለም የምግብ ፕሮግራም (WFP) በኮንጎ ኪንሻሣ ቡካቩ የሚገኘው የእህል መጋዘኑ መዘረፉን በብርቱ አወገዘው፡፡


የተዘረፈው እህል በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል በተባባሰው ጦርነት ተፈናቅለው ችግር ለጠናባቸው ዜጎች እንዲከፋፈል የታለመ ነበር መባሉን አናዶሉ ፅፏል፡፡


የተዘረፈው እህል ሰብአዊ ቀውሱን እንደሚያባብሰው ተገምቷል፡፡


የኮንጎ ኪንሻሣ ምስራቃዊ ክፍል በመቶዎች የሚቆጠሩ አማጺ በእና ታጣቂ ቡድኖች መርመስመሻ ነው፡፡


ታዲያ አሁን የM 23 አማጺ ቡድን በምስራቃዊ የአገሪቱ ክፍል ጥቃቱን እያፋፋመ ነው ፡፡


በሩዋንዳ ይደገፋል የሚባለው M 23 ከአማጺያ ሁሉ ሀይሉ ሆኖ ይጠቀሳል፡፡


የአለም የምግብ ፕሮግራም ተፋላሚዎቹ ለእህል መጋዘኖቹ እና ለድርጅቱ ሰራተኞች ደህንነት መረጋገጥ ከበሬታ እንዲኖራቸው መጠየቁን መረጃው አስታውሷል፡፡



የአሜሪካ እና የሩሲያ ሹሞች የዩክሬይኑ ጦርነት በሚቆምበት መላ በሳውዲ አረቢያ መነጋገር ጀመሩ፡፡


ንግግሩ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የአሜሪካው አቻቸው ማርኮ ሩቢዮም የተደመሙበት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


የዩክሬይንም ሆነ የአውሮፓ አገሮች ተወካዮች የንግግሩ ተካፋዮች አይደሉም ተብሏል፡፡


አውሮፓውያን ከንግግሩ ተገልለናል በሚል ቅሬታ እንደገባቸው ይነገራል፡፡


የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ እኛ ባልተካፈልንበት በሚካሄድ ንግግር የሚደረስን ስምምነት በጭራሽ አንቀበልም ሲሉ ሰንብተዋል፡፡


የዩክሬይኑ ጦርነት ያለ ሁነኛ መፍትሄ ወደ 3ኛ አመቱ እየተቃረበ ነው፡፡



የሊባኖስ ሹሞች የኢራን አውሮፕላኖች እንዳይመጡባቸው የጣሉትን እገዳ በደፈናው አራዘሙት፡፡


ቀደም ሲል የሊባኖስ ሹሞች የኢራን አውሮፕላኖች እንዳይመጡባቸው እስከ ዛሬ እገዳ ጥለው እንደነበር ገልፍ ኒውስ አስታውሷል፡፡


አሁን እገዳው በደፈናው ማራዘማቸው ተጠቅሷል፡፡


እገዳው መቼ እንደሚነሳም የተቀመጠ የጊዜ ገደብ የለም ተብሏል፡፡


በእገዳው ትዕዛዝ መሰረት ወደ ሊባኖስ የሚበርም ሆነ ወደ ኢራን የመልሶ ጉዞ የሚያደርግ አውሮፕላን እንደማይኖር ታውቋል፡፡


ሊባኖስ በሔዝቦላህ ታጣቂ ቡድን ምክንያት እስራኤል ባካሄደችው የጦር ዘመቻ ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባት ይነገራል፡፡


ሔዝቦላህ ደግሞ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪክ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comentarios


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page