top of page

የካቲት 12፣2016 - ከኢትዮጵያዊያን ለመግቢያ ብዬ ሰባራ ሳንቲም አልቀበልም ስትል ኬንያ ተናገረች

ወደ እኔ ከሚመጡ ኢትዮጵያዊያን ለመግቢያ ብዬ ሰባራ ሳንቲም አልቀበልም ስትል ኬንያ ተናገረች።


ወደ ኬንያ የሚገቡ ኢትዮጵያዊያን የጉዞ ፍቃድ ማረጋገጫ ክፍያ እንዳይከፍሉ መወሰኑን በተመለከተ የሀገሪቱ የሀገር ውስጥ ሚኒስቴር እና ብሔራዊ አስተዳደር ያወጣውን መረጃ በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ አረጋግጠዋል።


ወደ ኬንያ የሚሄዱ አፍሪካዊያን ካለፈው ጥር ወር ጀምሮ ሙሉ ለሙሉ ቪዛ መጠየቃቸውን የሚያስቀር አሰራር ስራ ላይ ማዋል መጀመሩ ይታወሳል።


በዚህ አሰራር ግን ተጓዧች የጉዞ ፍቃድ ፎርም መሙላት እና ክፍያ መፈፀም ይጠበቅባቸዋል።


ይህ የናይሮቢ አዲሱ አሰራር ለኢትዮጵያዊያን ተጓዦች ችግር መፍጠሩ ይታወሳል፡፡


ለጉብኝት፣ ለህክምና ለመሳሰሉት ወደ ኬንያ የሚሄዱ ኢትዮጵያዊያን ሀገራቱ የምትጠይቀውን የኦላይን ክፍያ ለመፈፀም እንደ ቪዛ የመሳሰሉ የክፍያ መፈፀሚያ ባለመስፋቱ ለመክፈል በብርቱ ተቸግረዋል፡፡


ከአፄ ሀይለስላሴ ዘመነ መንግስት ጀምሮ ሁለቱ ሀገራት በገቡት ስምምነት መሰረት ኢትዮጵያዊያን ያለ ቪዛ ጥየቃ ወደ ናይሮቢ ሲጓዙ ቆይተዋል፡፡


ከጥር ወር ጀምሮ ተግባራዊ የተደረገው የሀገሪቱ አዲሱ አሰራር በድጋሚ እንዲታይ ኢትዮጵያ ለኬንያ ጥያቄ ማቅረቧ የሚታወስ ሲሆን ጥያቄዋም ተቀባይነት ማግኘቱ ተሰምቷል፡፡


በኬንያ የኢትዮጵያ አምባሳደር ጀነራል ባጫ ደበሌ በኤክስ ገፃቸው ላይ ባወጡት ፅሁፍ ኬንያ የጉዞ ፍቃድ ማረጋገጫ ክፍያን ከኢትዮጵያዊያን ተጓዦች ላይ አንስታለች ብለዋል፡፡


ተጓዞች በኦላይን የሚሞላውን ቅፅ ወይንም ፎርም ግን አስቀድመው መሙላት እንደሚጠበቅባቸው አምባሳደሩ አሳስበዋል፡፡


ኢትዮጵያዊያን ያለምንም ክፍያ ወደ ኬኒያ እንዲገቡ በመፍቀዱም ለሀገሪቱ ምስጋና አቅርበዋል፡፡


ከኢትዮጵያ በተጨማሪ የኮሞሮስ፣ የኮንጎ፣ የኤርትራ፣ የሞዛምቢክ፣ የሳንማሪኖ እና ደቡብ አፍሪካ ዜጎችም ወደ ኬንያ ሲገቡ የጉዞ ፍቃድ ማረጋገጫ ክፍያ እንደቀረላቸው ኬንያ ወስናለች፡፡


ንጋቱ ሙሉ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



Comments


bottom of page