top of page

የካቲት 13፣2016 - የዳኞች ቁጥር ማነስን ጨምሮ የገጠሙን ችግሮችን ለመፍታት እየጣርን ነው ሲሉ ማዕከላዊና ደቡብ ምዕራብ ክልሎች ተናገሩ

የዳኞች ቁጥር ማነስን ጨምሮ የገጠሙን ችግሮችን ለመፍታት እየጣርን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎች ተናገሩ፡፡


በቀድሞው የደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ጉዳያቸው እየታዩ እና ፍርድ ያልተበየነባቸው የፍርድ ቤት መዝገቦች መጀመሪያ ወደተመሩበት አካባቢዎች ተልከዋል ተብሏል፡፡


በዚህ ሂደት የበዛ የጊዜ ቀጠሮ እየተሰጠባቸው፣ በእንጥልጥል የቀሩ እና ፍርድ ያልተሰጠባቸው የክስ መዝገቦች መኖራቸው ሸገር ከባለጉዳዮች ሰምቷል፡፡


ጉዳያቸው በቀድሞ ደቡብ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት እየታየላቸው የነበሩ ባለጉዳዮች ባጠረ ጊዜ ፍርድ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡


ፍርድ ያለተሰጠባቸው የክስ መዝገቦችን ባጠረ ጊዜ ዉሳኔ ለመስጠት የዳኞች ቁጥር ማነስ ችግር ሆኖብናል ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ኤርሲኖ አቡሬ ለሸገር ነግረዋል፡፡


ክልሉ እንደ አዲስ ቢሮዎችን እያደራጀ፣ መዝገብና ሌሎች አስፈላጊ ቁሳቁሶችን ከሀዋሳ ወደ አዲሱ ቢሮ ሀላባ ለማጓጓዝ የወሰደባቸው ጊዜያት የፍርድ ሂደቶቹ በጊዜያቸው እንዳይታዩ ያደረጉ ተጨማሪ ምክንያቶች ናቸው ሲሉ ኤርሲኖ ተናግረዋል፡፡


የፍርድ ቤት መዝገቦቹ እልባት እንዲያገኙና ባለጉዳዮች የበለጠ እንዳይጉላሉ በክልሉ በ4 ማዕከሎች ተዘዋዋሪ ችሎቶችን በመሰየም የሰበር እና የይግባኝ መዝገቦች እየታዩ ነው ተብሏል፡፡


ተዘዋዋሪ ችሎቶቹ እየሰሩ ያሉባቸው ከተሞች ሆሳዕና፣ ወልቂጤ፣ ቡታጅራ እና ወራቤ እንደሆኑም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕ/ት አውርተውናል፡፡



የደቡብ ምዕራብ ክልል በበኩሉ በክልሉ በፍርድ ሂደት ላይ የሚታዩ ችግሮችን በጥናት ለይቻለሁ በሏል፡፡


የዳኞች ቁጥር ማነስ የዚህኛውም ክልል ችግር እንደሆነ የክልሉ ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝደንት ቆጭቶ ገብረማርያም ነግረውናል፡፡


የዳኞች ቁጥር ማነስ የፍርድ ሂደቶችን ከማጓተቱም በላይ በሚሰጡ ፍርዶች ጥራት ላይም አሉታዊ ተፅዕኖ አለው ሲሉም የጠቅላይ ፍርድ ቤቱ ፕ/ት ተናግረዋል፡፡



በወረዳ፣ በዞን እና በክልል ደረጃ ያለውን የሰው ሀብት እጥረት ለመፍታት እየሞከርን ነው፡፡


በቅርቡም በየፍርድ ቤቶች የሚመደቡ የ66 ዳኞችን ሹመት አፅድቀናል ብለውናል፡፡



ማንያዘዋል ጌታሁን



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…




Comments


bottom of page