‘’በአማራ ክልል የታሰበው የምክክር ሂደት እንዲካሄድ እና ተጨባጭ ውጤት እንዲመጣ መንግስት በልበ ሰፊነት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለን እናምናለን’’ ሲል የምክክር ኮሚሽን ተናግሯል፡፡
በክልሉ በትጥቅ ትግል ውስጥ ያሉትን ከመንግስት ጋር ለማነጋገር ኮሚሽኑ በ3ተኛ ወገንም በጠረጴዛ ዙሪያ ችግራቸውን ለመፍታት አመቻቻለሁ የሚል ጥሪ አቅርቦ የነበረ ቢሆንም በመርህ ደረጃ የተቀበለው አባል አለማግኘቱን ተናግሯል፡፡
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በአማራ ክልል ያለው ጦርነት ለምክክሩ አስቻይ ነው ወይ? የሚል ጥያቄ ከጋዜጠኞች ቀርቦላቸው ነበር፡፡
ኮሚሽነሩ ይህ ጥያቄ የቀረበላቸው ኮሚሽኑ የ3 ዓመት የስራ ክንውን ሪፖርቱን ለጋዜጠኞች በቀረበበት ወቅት ነው፡፡
በሰጡት ምላሽም በክልሉ ያለው ህዝብ ምክክር እንዲደረግ እንደሚፈልግ የተናገሩት ኮሚሽነሩ ነገር ግን በአማራ ክልል አሁንም መንግስት እንደ መንግስት ካለበት የተደራራቢ ኃላፊነት አንፃር በልበ ሰፊነት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ እንዳለበት ተናግረዋል፡፡
መንግስት አንዳንድ እርምጃዎችን መውሰድ አለበት ብለን እናምናለን እኔም በግል አምናለው ብለዋል ኮሚሽነር መላኩ፡፡

መንግስት እርምጃ ይውሰድ ከማለት ውጪ በዝርዝር ያሉት ነገር የለም፡፡
ምክክሩ የተሳካ እና ውጤታማ እንደሆነ መንግስት አስቻይ ሁኔታዎችን መፍጠር እንዳለበት የተናገሩት ኮሚሽነሩ ከመንግስትም ይሁን በኩል ምክክሩ የበለጠ ተጨባጭ ለማድረግ የሚጠበቁ ነገሮች አሉ ብለዋል፡፡
ይህ ማለት ግን ሌሎች አይጠበቅባቸውም ማለት እንዳልሆነም ኮሚሽነሩ በንግግራቸው አስረድተዋል፡፡
ከአንድ ወገን ብቻ በሚዘረጋ እጅ ሊከናወን የሚቻል ነገር አይደለም ሲሉ የተናገሩት ኮሚሽነር መላኩ ወልደማርያም በመንግስትም ይሁን በታጣቂዎች በኩል ፈቃደኝነት መኖር አለበት ብለዋል፡፡
ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖች ናቸው ወደ ጫካ የገቡት እውነተኛ ጥያቄ የህዝብ ከሆነ ወደ ጠረጴዛ የማይመጣበት ምንም ምክንያት የለም ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ኮሚሽኑ በተደጋጋሚ በተለየ መልክ ጥያቄ አለን የሚሉ ወገኖችን ኑ ነው ያለው ያሉት ኮሚሽነር መላኩ በሌላ ሃገርም ቢሆን ድርድር ሊደረግ የሚችልበትን ሁኔታ የተቻለውን ያክል ኮሚሽኑ ያመቻቻል ብሎ ተናግሯል እስካሁን ግን ቢያንስ በመርህ ደረጃ እንኳን እንቀበል ብሎ ወደፊት የመጣ የለም ብለዋል፡፡
ሌላው ለኮሚሽኑ ከጋዜጠኞች የቀረበላቸው ጥያቄ ከህዝብ የሰበሰባቹሁትን አጀንዳ መንግስት የመፈፅም ፍላጎት ከሌለው ምን ታደርጋላቹ የሚል ሲሆን ኮሚሽነር መላኩ በሰጡት ምላሽ መንግስት የመፈጸም ግዴታ አለበት ምክኒያቱም በምክክር ሂደቱ የኢትዮጵያ ህዝብ ሃብቱን ጉልበቱን እውቀቱን እና ገንዘቡን አፍሶበታል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
በተመሳሳይ ለጥያቄው ምላሽ የሰጡት የአገራዊ ምክክር ኮሚሽነር ዮናስ አዳዬ(ዶ/ር) ጨው ለራስህ ስትል ጣፍጥ የሚለውን አገራዊ አባባል በመጥቀስ መንግስት በራሱ ተማምኖ ነው አገራዊ ምክክር ያስፈልገኛል ያለው ስለዚህ የቀረበለትን ሀሳብ ስራ ላይ ማዋል አለበት፣ ካላዋለ የህዝብ ውክልና ያለው ስለሆነ ውክልናውን እንዳይነፈግ አብረን ሆነን እንጠይቃለን ብለዋል፡፡
ያሬድ እንዳሻው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5r
Yorumlar