top of page

የካቲት 15፣2016 - አለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ለዘመን ባንክ የ30 ሚሊዮን ዶላር መተማመኛ ለመስጠት ተስማማ

  • sheger1021fm
  • Feb 23, 2024
  • 2 min read

በዘመን ባንክ በኩል ለሚደረጉ አለም አቀፍ ንግዶች የአለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን(IFC) የ30 ሚሊዮን ዶላር መተማመኛ ለመስጠት ተስማማ።


ስምምነቱም በዘመን ባንክ ዋና መስሪያ ቤት በባንኩ ዋና ስራ አስፈፃሚ ደረጀ ዘበነ እና በአለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የኢትዮጵያ ቢሮ ሃላፊ ማዳሎ ሚኖፉ ተፈርሟል።


በዓለም አቀፍ ንግድ ውስጥ የግብይት ስርዓት መዛባት ሲያገጥም፣ በሽያጭ እና ገዢ መካከል አለመተማመን ሲኖር ባንኮች እምነት እንዲጣልባቸው ጥሬ ገንዘብ በመመደብ ጭምር ድጋፍ ያደርጋሉ ተብሏል።


ይህ ደግሞ በባንኮች ላይ ጫና እንደሚፈጥር ያስረዱት የዘመን ባንክ ስራ አስፈፃሚ ደረጀ ዘበነ ይህ በኢትዮጵያ የፀጥታ ችግር ባጋጠመባቸው ወቅቶች ጎልቶ ታይቷል ብለዋል።



በዚህ ስምምነት መሰረት የአለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን የዘመን ባንክን የትሬድ ፋይናንስ (የወጪና ገቢ ንግድ ገንዘብ አቅርቦት) እንቅስቃሴ ለማጠናከርና በኢትዮጵያ ላሉ የወጪ ንግድ ላይ ለሚሰሩ ድርጅቶች አዲስ የንግድ ትስስርን ለመፍጠር የ30 ሚሊዮን ዶላር ዋስትና ያቀርባል ተብሏል።

ፕሮግራሙ ለባንኩ የንግድ ፋይናንስ ድጋፍ በማቅረብ የኢትዮጵያን የወጪና ገቢ ንግድ ለመደገፍ ብሎም አህጉራዊ ንግድን ማበረታታትን አላማው ያደረገ ነው ሲባል ሰምተናል።


ስምምነቱ ዓለም አቀፋዊ የኢኮኖሚ አለመረጋጋት በሚኖርበት ወቅት በገቢና ወጪ ንግድ ላይ የተሰማሩ የንግድ አጋሮችንም ሆነ የባንኩን ስጋት በእጅጉ እንደሚቀንስ የዘመን ባንክ ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት አቶ ደረጀ ዘበነ አስረድተዋል፡፡


ይሀ ፕሮግራም የወጪ ንግድ ፋይናንስ እንዳይስፋፋ የሚገድቡ እከሎችን ወይም ለዘርፉ ፈታኝ የሆኑ ስጋቶችን ለመቀነስ የሚረዳ ነው ተብሎለታል።


ለወጪና ገቢ ንግድ ዘርፍ ፋይናንስ የማቅረብ አቅምንም ያሰፋል ሲባልም ሰምተናል።


ዘመን ባንክ ባንክ ከዓለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን ያገኘው የ30 ሚሊዮን ዶላር የአለም አቀፍ ንግድ ዋስትና፤ ኮርፖሬሽኑ ለአፍሪካ ሀገራት መሰል ስራ ብሎ የያዘው 1 ቢሊዮን ዶላር አካል መሆኑ ተነግሯል።


ከዘመን ባንክ ጋር በአጋርነት ለመስራት የተፈራረመው አለም አቀፉ የፋይናንስ ኮርፖሬሽን፤ የዓለም ባንክ አባል ሲሆን በማደግ ላይ ያለውን የግል ዘርፍ ላይ የተለየ ትኩረት በማድረግ የሚደግፍ የልማት ተቋም መሆኑን ሰምተናል፡፡

ባለፈው ዓመት ብቻ በማደግ ላይ ባሉ ሀገሮች ለሚካሄዱ የግል ኩባንያዎችና የገንዘብ ተቋማት 43.7 ቢልዮን የአሜሪካ ዶላር አበርክቷል ተብሏል፡፡



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page