የካቲት 17 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች
- sheger1021fm
- Feb 24
- 1 min read
የሊባኖሱ የጦር ድርጅት(ሔዝቦላህ) የቀድሞ መሪ የሐሰን ናስረላህ የቀብር ስነ ሥርዓት ትናንት ተፈፀመ፡፡
ናስረላህ ከመንፈቅ በፊት እስራኤል በሊባኖሷ ርዕሰ ከተማ ቤይሩት በፈፀመችው የአየር ድብደባ መገደላቸውን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ከጥቂት ወራት በፊት በተኩስ አቁም እስከተገታ ድረስ እስራኤል በሊባኖስ የተለያዩ ክፍሎች ጥቃት ስታደርስ ቆይታለች፡፡
ከናሰረላህ የቀብር ሥነ ሥርዓት መፈፀም በፊት በቤይሩት ትልቅ ስታዲዮም የሐዘን መታሰቢያ ተደርጎላቸዋል፡፡
በሥነ - ሥርዓቱም የሔዝቦላህ አባላትን ጨምሮ በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተገኝተዋል፡፡
የናስረላህ ምክትል የነበሩት የሐሺም ሳፈዲንም የቀብር ሥነ-ሥርዓትም አብሮ መፈፀሙ ታውቋል፡፡

በጀርመን በተካሄደው ምርጫ የወግ አጥባቂዎች (CDU/CSU) የፖለቲካ ማህበር በመሪነት አጠናቀቀ፡፡
የወግ አጥባቂዎቹ የፖለቲካ ማህበር በምርጫው በመሪነት ያጠናቀቀው ከተሰጠው ድምፅ የ28 ነጥብ 6 በመቶ ውጤት በማግኘት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
አማራጭ ለጀርመን የሚሰኘው AFD የፖለቲካ ማህበር ደግሞ ሁለተኛ ሆኗል፡፡
SPD የተሰኘው ግራ ዘመም የፖለቲካ ማህበር 3ኛ ሆኖ አጠናቋል፡፡
በጀርመን ከጥቂት ወራት በኋላ በዚሁ የምርጫ ውጤት መሰረት አዲስ ጥምር መንግስት እንደሚቋቋም ታውቋል፡፡
የወግ አጥባቂዎቹ የፖለቲካ ማህበር የበላይ ፍሬድሪክ ሜርዝ የጀርመን ቀጣዩ መራሄ መንግስት ይሆናሉ ተብሏል፡፡
የየመን ሁቲዎች በአሜሪካ F 16 የጦር ጄት ላይ ከምድር ወደ አየር ተምዘግዛጊ ሚሳየል ተኮሱ ተባለ፡፡
ሁቲዎቹ በአሜሪካው የጦር አውሮፕላን ላይ ሚሳየል የተኮሱት ከ5 ቀናት በፊት እንደሆነ የፔንታገን ሹሞች መናገራቸውን ፎክስ ኒውስ መዘገቡን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡
በአሜሪካው የጦር አውሮፕላን ላይ በሁቲዎቹ ሚሳየል የተተኮሰበት በየመን የባህር ዳርቻ አቅራቢያ የአየር ክልል መሆኑ ታውቋል፡፡
ሆኖም አውሮፕላኑ በተተኮሰበት ሚሳየል አልተመታም ተብሏል፡፡
ሁቲዎቹ በአሜሪካ የጦር ጄት ላይ ሚሳየል ሲተኩሱ የመጀመሪያቸው እንደሆነ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር አጋሮች እና የፖለቲካ ሸሪኮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
እስራኤል በዌስት ባንክ በ3 የመጠለያ ጣቢያዎች ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ፍልስጤማውያንን አስወጣቻቸው፡፡
ፍልስጤማውያኑ እንዲወጡ የተደረጉባቸው በጀኒን ፣ ቱርካርም እና ኑር ሸምስ የሚገኙ መጠለያዎች እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
የእስራኤሉ የመከላከያ ሚኒስትር እስራኤል ጋትስ በአሁኑ ወቅት የመጠለያ ጣቢያዎቹ ሙሉ በሙሉ ከነዋሪዎች ነፃ መደረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
በእነዚህ መጠለያ ሰፈሮች የእስራኤል ወታደሮች እና ታንኮች እንደሚሰፍሩባቸው ታውቋል፡፡
የጋዛው ጦርነት በተኩስ አቁም ጋብ ካለ በኋላ የእስራኤል ጦር በዌስት ባንክ በሰፊ የጦር ዘመቻ ላይ ይገኛል ተብሏል፡፡
በዚህ ዘመቻም 40 ሺህ ፍልስጤማውያን ከየመጠለያው እንደተፈናቀሉ መረጃው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments