ተከታትለው በሚመጡት የዓብይ እና የረመዳን አጿማት ምክንያት የሚሰበሰበው የደም መጠን እንዳይቀንስ ስጋት አለኝ ሲል ብሔራዊ ደም እና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ተናገረ፡፡
በዚህ ጊዜ የደም እጥረት እንዳይኖር ከወዲሁ ከለጋሾች የማሰባሰቡ ስራ እየተሰራ እንደሆነ የብሄራዊ ደምና ህብረ ህዋስ አገልግሎት ምክትል ዋና ዳይሬክተር አቶ ሃብታሙ ታዬ ነግረውናል፡፡
የአገልግሎት መስሪያ ቤቱ ባለፉት ሰባት ወራት 240 ሺህ ዩኒት ደም ለማሰባሰብ አስቦ የነበረ ቢሆንም በተለይም በአማራ ክልል ባለው ግጭት ሳቢያ ለማሰባሰብ የቻለው ከ190 ዩኒት ደም ያልበለጠ ነው ተብሏል፡፡
ክልሉ ከዚህ ቀደም ብዙ ቁጥር ያለው ደም ይሰበሰብበት የነበረ መሆኑን የሚናገሩት ሃላፊው ግጭቱ ባስከተለው ጉዳት ደም ለሚፈልጉ ሰዎች መድረስ ያልተቻለበት ጊዜም እንደ ነበር አስረድተዋል፡፡
የዓለም ጤና ድርጅት ባስቀመጠው መስፈርት መሰረት በአንድ ሀገር በቂ የደም መጠን እንዲኖር ካስፈለገ ከአጠቃላይ የህዝቡ ቁጥር 1 በመቶው ደም መለገስ ይኖርበታል፡፡
በዚህ ስሌት በኢትዮጵያ በጥቂቱ ከ1 ሚሊዮን ዩኒት በላይ ደም መሰብሰብ ሲኖርበት በየዓመቱ የሚሰበሰበው ግን ከ4 መቶ ሺህ ዩኒት ያልበለጠ መሆኑን ሰምተናል፡፡
ምንታምር ፀጋው
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments