top of page

የካቲት 18 2017 - የካቲት 18 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Feb 25
  • 1 min read

 

የብዙዎቹ ምዕራባዊያን ሀገሮች መሪዎች ዩክሬይንን አይዞሽ አንቺን መደገፋችንን እንቀጥላለን አሏት፡፡

 

ትናንት በአስራዎች የሚቆጠሩ የምዕራባዊያን ሀገሮች መሪዎች በዩክሬይኗ ርዕሰ ከተማ ኪየቭ እንደተገኙ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡

 

የስዊድን፣ የኖርዌይ፣ የስፔን እና የዴንማርክ መሪዎች በኪየቭ ከተገኙት ከብዙ በጥቂቱ ናቸው፡፡

 

የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ጀስቲን ትሩዶውም በኪየቭ መገኘታቸው ተጠቅሷል፡፡

 

የምዕራባዊያን አገሮች መሪዎቹ ዩክሬይንን አለንልሽ ያሏት አዲሱ የአሜሪካ አስተዳደር ለዩክሬይን የሚሰጠው የጦር ድጋፍ መቀጠሉ በእጅጉ ባጠራጠረበት ወቅት ነው ተብሏል፡፡

 

በዩክሬይኑ ጦርነት የሩሲያ ጦር ፍፁም የበላይነቱን መጨበጡ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡

 

በአንፃሩ የዩክሬይን ጦር በስንቅ እና ትጥቅ እንዲሁም በተዋጊዎች እጥረት እየተፈተነ ነው ተብሏል፡፡


 

የሴኔጋል መንግስት እና የመገንጠል አቀንቃኝ የነበረው MFDC የተሰኘው አማጺ ቡድን የሰላም ስምምነት ተፈራረሙ፡፡

 

ሁለቱ ወገኖች የሰላም ስምምነት እንዲፈርሙ የሽምግልና ሚና የተጫወቱት የጊኒ ቢሳዎው ፕሬዘዳንት ኡማሮ ሲስኮ አምባሎ እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

MFDC ከ40 አመታት በላይ በትጥቅ አመፅ መቆየቱን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

ቡድኑ የሴኔጋልን ደቡባዊ ክፍል የመገንጠል አላማ ነበረው ተብሏል፡፡

 

አሁን በተደረሰው የሰላም ስምምነት መሰረት የትጥቅ አመፁን ለማቆም ግዴታ መግባቱ ታውቋል፡፡

 

የጊኒ ቢሳዎ መንግስት የሰላም ስምምነት እንዲደረስ ለተወጣው ድርሻ እየተመሰገነ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡

 

 

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ በሱዳን የRSF ፈጥኖ ደራሽ ሀይል በአገሪቱ ደባል መንግስት ለማቋቋም የሚያደርገው ሙከራ በእጅጉ አሳስቦኛል አሉ፡፡

 

ፈጠኖ ደራሽ ሀይሉ በኬኒያ ናይሮቢ በተከናወነ ሥነ ሥርዓት ከሱዳን የተለያዩ የፖለቲካ ወገኖች ጋር የሽግግር መንግስት መመስረት የሚያስችለውን ስምምነት መፈራረሙን አናዶሉ አስታውሷል፡፡

 

በጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን የሚመራው የሱዳን ወታደራዊ መንግስት የተቃዋሚዎቹ ደባል መንግስት በሱዳን ቦታ የለውም ሲል ሰንብቷል፡፡

 

የመንግስታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ የደባሉ መንግስት ምስረታ ግጭት አባባሽ ነው ማለታቸው ተሰምቷል፡፡

 

የሱዳን መንግስት ጦር ከፈጥኖ ደራሸ ሀይሉ ጋር ሲዋጋ ከአመት ከ10 ወራት በላይ ሆኖታል፡፡

 

ጦርነቱ ዓይነተ ብዙውን ሰብአዊ ቀውስ እያባባሰ መሆኑ ይነገራል፡፡

 

 

የተባበሩት መንግስታት የፀጥታው ምክር ቤት የዩክሬይኑ ጦርነት በአጣዳፊ እንዲቆም ጠየቀ፡፡

 

ምክር ቤቱ ጦርነቱ እንዲቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ማሳለፉን TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡

 

የውሳኔ ሀሳቡ በአሜሪካ ተረቅቆ የቀረበ መሆኑ ታውቋል፡፡

 

የውሳኔ ሀሳቡ ጦርነቱ የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን ማቋቋሚያ መርሆዎች መሰረት አድርጎ እንዲቆም የሚጠይቅ መንፈስን ያዘለ ነው ተብሏል፡፡

 

ምክር ቤቱ የዩክሬይኑ ጦርነት እንዲቆም የሚጠይቅ ውሳኔ ቢያሳልፍም ግሪክ ፣ ፈረንሳይ ፣ ስሎቬኒያ ፣ ዴንማርክ እና ብሪታንያ ድምፅ ተአቅቦ ማድረጋቸው ተጠቅሷል፡፡

 

በውሳኔ ሀሳቡ ላይ ስለ ዩክሬይን ግዛታዊ አንድነት ጉዳይ የሰፈረ ነገር እንደሌለ መረጃው አስታውሷል፡፡

 

በሩሲያ እና በዩክሬይን መካከል የሚካሄደው ጦርነት ትናንት 3ኛ ዓመቱን ደፍኗል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

 

Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page