ኢትዮጵያ ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆነው ሰው አሁንም ምግቡን የሚያበስለው ማገዶን ተጠቅሞ ነው ሲል የውሃ እና ኢነርጂ ሚኒስቴር ተናገረ።
የኤሌክትሪክ ሃይልን በመጠቀም ምግቡን የሚያበስለው ኢትዮጵያዊ 10 ከመቶ ብቻ ነው ተብሏል።
ይህ የተባለው የሶላር ሃይል ቴክኖሎጂ የምክክር መድረክና ኤግዚቢሽን በተከፈተበት ወቅት ነው።

ውሃና ኢነርጂ ሚንስትር ዴኤታ ኢንጅነር ሱልጣን ዋሌ ኢትዮጵያ ከውሃ፣ ጂኦ ተርማል፣ ነፋስና ፀሐይል ኃይልን በመጠቀም ታዳሽ የኤሌክትሪክ ሃይል የማመንጨት አቅም ቢኖራትም እስካሁን ግን ከ54 ከመቶ በታች ለሆነው ህዝቧ ነው ይህንን ማድረግ የቻለችው ብለዋል።
መንግስት ይህንን ክፍተት ለመሙላት በሚል የሃይል አቅርቦት ዘርፍ በተለይም ታዳሽ ሃይል ልማት ዘርፍን ለግሉ ባለሃብት ክፍት አድርጎታል፣ ይህንን እድል ኢንቨስተሮች ሊጠቀሙበት ይገባል ብለዋል።
በሃገር ውስጥ እድገት እንዲመጣ፣ ምርት እንዲጨምር ከተፈለገ አሁን የኤሌክትሪክ ሃይል ዋነኛ እና ግዴታ እየሆነ ነው የተባለ ሲሆን የኃይል አቅርቦት ችግርን ሳይፈቱ ዘላቂ ልማት ማረጋገጥ አይቻልም መባሉን ሰምተናል።
በረከት አካሉ
Comments