top of page

የካቲት 20 2017 ‘’የኤርትራ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎችን የኤርትራን ዜግነት ተቀበሉ ብሎ እያስገደዳቸው ነው’’

የኤርትራ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው ሁለት የኢሮብ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎችን የኤርትራን ዜግነት ተቀበሉ ብሎ እያስገደዳቸው መሆኑን በህዝብ የእምባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ተናገረ፡፡


በዚህም ምክንያት ህዝቡ አጣብቂኝ ውስጥ መግባቱንና ስራውንም መከወን እንዳልቻለ ጠቅሷል፡፡


ተቋሙ እንደነገረን ከሆነ ይህ ዓመት ከተጀመረ የተቀበለው የህዝብ አቤቱታ 83 ብቻ ነው፡፡


ከተቀበላቸው አብዛኞቹ ቅሬታዎች ከመቀሌና አካባቢው የመጡ ናቸው ይህም ምክንያቱ የትራንስፖርትና ተያያዥ ኢኮኖሚያዊ ችግሮች በመኖራቸው ነው ያሉን በህዝብ የእምባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ ፅህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑ አቶ ፀሐዬ አምባዬ ናቸው፡፡

ኃላፊው እንደሚሉት የኤርትራ ሰራዊት በተቆጣጠራቸው ሁለት የኢሮብ ወረዳዎች ያሉ ነዋሪዎችን የኤርትራን ዜግነት ተቀበሉ ብሎ እያስገደዳቸው ነው፡፡


ነዋሪዎቹ ህልውናቸው አደጋ ውስጥ ገብቷል፤ ገሚሱ ወደ አዲግራት እየሸሸ ነው ገሚሱ ደግሞ የሚመጣውን ለመጋፈጥ እዚያው ቀርቷል ብለውናል፡፡


በአካባቢዎቹ በርካታ ችግሮች ቢኖሩም ያሉበት ሁኔታ ወደ እምባ ጠባቂ ተቋም መጥተው አቤቱታቸውን ለማሰማት እንደማያስችላቸው አቶ ፀሐዬ ነግረውናል፡፡


ከዚህም በተጨማሪ በህውሃት መሪዎች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል ወደ ከተማና ወረዳ በመውረዱ ህዝቡ በሁለት ከንቲባዎች ለመመራት ተገዷል፤ ለማን አቤት ማለት እንዳለበት ግራ ተጋብቷልም ይላሉ፡፡


በክልሉ በተፈጠረው ችግር ምክንያት በደላችን ይሰማልን እምባችንም ይታበስልን ከሚሉ አቤት ባዮች አቤቱታዎችን ለመቀበል መቸገሩን የሚናገረው የእምባ ጠባቂ ተቋም የመቀሌ ቅርንጫፍ፤ የህውሃት መሪዎች ተነጋግረው ችግራቸውን ካልፈቱ ክልሉ መንግስት አልባ ሊሆን እንደሚችል ሃላፊው አቶ ፀሐዬ አምባዬ ነግረውናል፡፡


አጣብቂኝ ውስጥ ያሉት በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር ያሉ ነዋሪዎች በፌድራል መንግስቱ መፍትሄ ሊሰጣቸው ይገባል ብለዋል፡፡


በዚህ ዓመት ወደ ተቋሙ ከመጡ 83 አቤቱታዎች ተቋሙን የሚመለከቱት 29ኙ ናቸው፤ ከዚህም ውስጥ 24ቱ መፍትሄ አግኝተዋል 5ቱ በሂደት ላይ ናቸው ተብሏል፡፡


ቀሪዎቹ 54ቱ ተቋሙን የማይመለከቱ በመሆናቸው ውድቅ ተደርገዋል፡፡


ከአቤቱታዎቹ የሚበዙት ከአሰሪና ሰራተኛ ጋር የተያያዙ ቅሬታዎች ሲሆኑ በአገልግሎት አለመርካት እንዲሁም የመሬት ይዞታን የተመለከቱ እንደሆኑም ሰምተናል፡፡


ምንታምር ፀጋው


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page