top of page

የካቲት 21፣2016 -  የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ገበያውን በተዓማኒነትና በብቃት እንዲመራ በብርቱ ይረዳሉ የተባሉ የተለያዩ ስምምነቶች ዛሬ አድርጓል፡፡

የተደረገው ስምምነት የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለስልጣን የካፒታል ገበያ መሠረተ ልማቶችን ለማበርታት ግልጽነት እንዲሁም የቴክኖሎጂ አቅምን ለማዳበር ያግዛሉ መባሉንም ሰምተናል፡፡

 

ዛሬ ይህንኑ ስራ በህብረት አብሮ ለማስጓዝ የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ብሩክ ታዬ፣ የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን  ምክትል ኮሚሽነር  ዘላለም መንግስቴ፣ የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረና የፍትህ ሚኒስትር ሚኒስትር ዶ/ር ጌድዮን ጢሞቲዮስ ተሰባስበዋል፡፡

 

በተጠቀሱት አራት ተቋማት የሚመሩት የጋራ ግብረ ሀይልም ተቋቁሟል፡፡

 

የካፒታል ገበያ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ዶር ብሩክ ታዬ ገበያው አዲስ እንደመሆኑ በገበያው ውስጥ በረቀቀ መልኩ ወንጀል ሊሰራ እንደሚችል ታሳቢ በማድረግ የሚመለከተው ሁሉ በካፒታል ገበያ ሊፈፀም የሚችሉ ነገሮችን ወጥ በሆነ መንገድ በማየት አብረን እንሰራለን ብለዋል፡፡

 

የዚህ ግብረ ሀይል ዋናው ስራው ገበያው ተአሚነት እንዲኖረው በብርቱ ያግዛል መባሉን ሰምተናል፡፡

 

በአክሲዮን ጉዳይ ከህግ ወጣ ብለው ሲሰሩ የነበሩት ሁሉ  እስካሁን ሲመከሩ ነበር  ይህ ግብረሀይል መቋቋሙ ወደ ህጋዊ መስመር እንዲገቡ ለእነሱም መልዕክት ነው  መባሉን ሰምተናል፡፡

 

በዚህ ግብረሀይል መቋቋም ስምምነት ላይ ሁሉም በገበያው ህግና ሥርአት አክብረው እንዲሰሩ ተብሏል፡፡

 

የፍትህ ሚኒስትሩ ጌድዮን ጢሞቲዮስ በገበያው ከመመሪያ ውጪ የሚሰሩ በሙሉ የአስተዳደር ቅጣት ሳይሆን ከበድ ያለ የወንጀል ቅጣት ሊያስከትል እንደሚችል በጥብቅ አሳስበዋል፡፡

 

የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ም/ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ በገበያው ያለፈቃድና ከህግ ውጪ የሚሰሩ በሙሉ፤ በወንጀል እንዲጠየቁ ይደረጋልም ብለዋል፡፡

 


ግብረ ኃይሉ ማጭበርበር ባለበት ሁኔታ እና በሕገወጥ የአከሲዮን አቅርቦት ላይ የተሰማሩ  በርካታ ኢንቨስተሮች ገንዘባቸውን እንዲያጡ ምክንያት የሆኑ አክሲዮን ሻጮችን በመለየት ለፍርድ የማቅረብ ኃላፊነት አለበት ተብሏል።

 

በተያያዘም የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣንን በቴከኖሎጂ ለመደገፍም የትብብር ስምምነት ተደርጓል፡፡

 

 የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት አጀንሲ ፣ የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት እና የኢትዮጵያ ብሔራዊ መታወቂያ አገልግሎት ዋና ዳይሬክተሮች በጉዳዩ ላይ ማብራሪያ ሰጥተዋል አብረው ለመስራትም ተስማምተዋል።

 

የፋይናንስና ደህንነት መረጃ ዋና ዳይሬክተር አቶ ሙሉቀን አማረ የካፒታል ገበያው በሀሰተኛና ምንጩ ባልታወቀ ገንዘብ እንዳይጥለቀለቅ  በተቀናጀ መልኩ ጥብቅ  መረጃ በመቀባበል በብርቱ እንደሚሰራ ተናግረዋል፡፡

 

 ከሳይበር ደህንነት ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ባለስልጣኑን ለመጠበቅና አቅሙን ለማሳደግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂን በመጠቀም ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን  ለመከታተል እና ለመቅረፍ የሚመለከታቸው ሁሉ አብረውለመስራት ተስማምተዋል፡፡

 

እነዚህ ስምምነቶች የኢትዮጵያ የካፒታል ገበያ ባለሥልጣን  ከተሰጡት ሥልጣን እና ተግባራት ዓላማ በቀጥታ ከመደገፍም ባለፈ ለኢንቨስተሮች ተገቢውን ጥበቃ ወይም ከለላ ለመስጠት የሚረዳም ነው ተብሏል።

 

 

ተህቦ ንጉሴ

 


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

 

 

 

Comments


bottom of page