top of page

የካቲት 22 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Mar 1
  • 2 min read

የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ በዋይት ሐውስ ከአሜሪካ መሪዎች ጋር ያደረጉት ንግግር በጭቅጭቅ እና ባለመግባባት ተጠናቀቀ፡፡


ዜሌንስኪ የዩክሬይን ጦርነት በሚቆምበት ጉዳይ ከአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እና ከምክትላቸው ጄዲ ቫንስ ጋር ቢነጋገሩም በጭራሽ ሊግባቡ እንዳልቻሉ የተለያዩ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል፡፡


ትራምፕ የዩክሬይኑ ፕሬዘዳንት ለሰላም ደፈር ያለ እርምጃ እንዲወስዱ ተጭነዋቸዋል ተብሏል፡፡


ዜሌንስኪ በፊናቸው የደህንነት ዋስትና ሊሰጠን ይገባል በሚል አቋማቸው ፀንተዋል፡፡


ትራምፕ ዜሌንስኪን በ3ኛው የአለም ጦርነት እየቆመርክ ነው ሲሉ ወርፈዋቸዋል፡፡


ቀደም ሲል ብዙ የተነገረለት የአሜሪካ እና የዩክሬይን ማዕድን ነክ ስምምነት ሳይፈረም መቅረቱ ታውቋል፡፡


ሰሞኑን የአሜሪካ እና የዩክሬይን ግንኙነት ድፍርስርሱ እየወጣ መሆኑ ይነገራል፡፡


ጭቅጭቅ ባልተለየው ድባብ የአሜሪካው ምክትል ፕሬዘዳንት ጄዲ ቫንስም የዩክሬይን ፕሬዘዳንት በግላጭ ምስጋና ቢስ ሲሏቸው ተሰምቷል፡፡



PKK የተሰኘው የኩርዶች አማጺ ቡድን ትጥቅ ፈትቶ ከቱርክ መንግስት ጋር ሰላም እንዲያወርድ የቀረበለት ጥሪ እኔን አይመለከትም ሲል SDF የተሰኘው የሶሪያ ኩርዶች ቡድኖች አማጺ ቡድን ተናገረ፡፡


የቱርክ መንግስት SDFንም የPKK አንድ አካል አንድ አምሳል አድርጎ እንደሚቆጥረው ሚድል ኢስት ሞኒተር ጽፏል፡፡


PKK ትጥቅ ፈትቶ ከቱርክ መንግስት ጋር ሰላም እንዲያወርድ ጥሪ ያቀረቡት በቱርክ በእስር ላይ የሚገኙት መሪው አብደላ ኦቻላን ናቸው ተብሏል፡፡


PKK ከቱርክ የተነጠለች ኩርዲስታንን መመስረትን አልሞ ላለፉት 40 አመታት የትጥቅ አመፅ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡


በሰሜናዊ ሶሪያ የሚንቀሳቀሰው SDFንም የኩርዶች የጦር ድርጅት መሆኑ ይነገራል፡፡


ቱርክ SDF የPKK አንድ አካል አንድ አምሳል ነው ትላለች፡፡



በኮንጎ ኪንሻሣ ምንነቱ በውል ያልተለየው ሰውነት ደም መፍሰስ አስከታይ ወረርሽኝ አሁንም ድረስ መነሻ ምክንያት አልተለየም ተባለ፡፡


ወረርሽኙ በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ክፍል 5 መንደሮች ከ60 ያላነሱ ሰዎችን እንደገደለ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡


የአለም የጤና ድርጅት የአፍሪካ ቅርንጫፍ ወረርሽኙ በውሃ መበከል ምክንያት የመጣ ሳይሆን አይቀርም ማለቱ ተሰምቷል፡፡

ይሄም ገና ከመላ ምት ያልዘለለ ነው፡፡


ከ1 ሺህ በላይ ሰዎች በበሽታው ተይዘው እንደሚገኙ ተጠቅሷል፡፡


በሽታው ከሰውነት ደም መፍሰስ አስከታይነቱ በተጨማሪ ከፍተኛ ትኩሳት ፣ የራስ ምታት የጡንቻ መዛል እና የመሳሰሉ ምልክቶችን ያሳያል ተብሏል፡፡


ከኢቦላ እና ማርበርግ ጋር ተመሳሳይ ምልክቶችን ያሳያል፡፡


ይሁንና ኢቦላም ማርበርግም እንዳልሆነ እየተነገረ ነው፡፡



አሜሪካ የሩሲያ አምባሳደሯን እወቁልኝ ማለቷን የክሬምሊን ሹሞች ተናገሩ፡፡


በሩሲያ የአሜሪካ አምባሳደር በመሆን የተሰየሙት አሌክሳንደር ዳርቺየቭ የተባሉ ዲፕሎማት እንደሆኑ አናዶሉ ፅፏል፡፡


በአሁኑ ወቅት ሩሲያ እና አሜሪካ በግንኙነት ማሻሻያ ሒደት ላይ ናቸው፡፡


ሰሞኑንም በዚሁ ጉዳይ የሁለቱ አገሮች ልዑካን በቱርክ ኢስታምቡል እንደተነጋገሩ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


አሜሪካ በአምባሳደርነት የሰየመቻቸው ዳርቪየቭ በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት የመምሪያ ሀላፊ ነበሩ ተብሏል፡፡


በቅርቡም በሩሲያ የአምባሳደርነታቸውን ተልዕኮ መወጣት እንደሚጀምሩ መረጃው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page