የአውሮፓ ህብረት የውጭ ጉዳይ ሀላፊ ጆሴፍ ቦሬል የእስራኤል የጋዛ ዘመቻ ሰርጡን ከነጭራሹ ወደ ምድረ በዳነት የመለወጥ ይመስላል አሉ፡፡
ጆሴፍ ቦሬል በእስራኤል የጋዛ ዘመቻ ፍልስጤማውያን ለአመታት ያፈሩት ሁሉ እየተደመሰሰ ነው ብለዋል፡፡
እስራኤል የጋዛ ዘመቻዬ በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ነው እንደምትል ቦሬል አንስተዋል፡፡
ያም ሆኖ የእስራኤል የጋዛ የጦር ይዞታ ከዚያም የዘለለ ነው ማለታቸው አናዶሉ ፅፏል፡፡
እስራኤል ዛን በአጠቃላይ መኖር ወደማይቻልበት ስፍራነት እየለወጠችው ነው ብለዋል፡፡
የእስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻ ዛሬ 5ኛ ወሩን ደፍኗል፡፡
በምስራቅ ዩክሬይን በተለያዩ አቅጣጫዎች የሩሲያ ጦር ማጥቃት እየተፋጠነ ነው ተባለ፡፡
የበርካታ ከተሞች ነዋሪዎቸች ፍርሃት እና ስጋታቸው እያየለ መምጣቱን እንደተናገሩ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከሳምንታት በፊት የሩሲያ ጦር የአቭዲቭካ ከተማን ከዩክሬይን ሰራዊት መቀማቱን ዘገባው አስታውሷል፡፡
ከዚያ ወዲህ የሩሲያ ጦር በብዙ አቅጣጫዎች ወደ ምዕራብ እየገሰገሰ ነው ተብሏል፡፡
የዩክሬይን ጦር እየተከላከልኩ ነው ቢልም በተግባር የሚታየው በተቃራኒው እንደሆነ የብዙ ከተሞች ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል፡፡
የሩሲያ እና የዩክሬይን ጦርነት ከ2 አመታት በላይ ሆኖታል፡፡
የየመን ሁቲዎች ንብረትነቷ የአሜሪካ ኩባንያ የሆነችን የንግድ መርከብ መትተው ጉዳት ማድረሳቸው ተሰማ፡፡
ጥቃት የተሰነዘረባት መርከብ የባርባዶስን ሰንደቅ ዓላማ የምታውለበልብ እንደሆነች አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ይሁንና በመርከቧ ላይ የደረሰው የጉዳት መጠን በዝርዝር ባይጠቀስም 3 ባሕረኞቿ ሲገደሉ 4 ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
የአሜሪካዋ የንግድ መርከብ ጥቃቱ የደረሰባት በኤደን ወደብ አቅራቢያ መሆኑ ታውቋል፡፡
ሁቲዎቹ በቃል አቀባያቸው አማካይነት እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን እስካላቆመች እና በዚያ ላሉ ፍልስጤማውያን ሰብአዊ እርዳታ እንዲገባ እስካልፈቀደች ድረስ መሰል ጥቃታችን ይቀጥላል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የየመንን ሰሜናዊ ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የፖለቲካ ወዳጆች እና የጦር አጋሮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
የሔይቲ የፀጥታ መደፍረስ እየተባባሰ ነው ተባለ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሔነሪ ወደ አገር ቤት መመለስ እንዳልቻሉ ሜይል ኦን ላየን ፅፏል፡፡
የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች በርዕሰ ከተማዋ ፖርቶ ፕሪንስ የሚገኘውን ኤርፖርት ሊይዙት ተቃርበዋል ተብሏል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ አገር ለመመለስ ቢሹም በጎረቤት ዶሜኒካን ሪፖብሊክ እሳቸውን ያሳፈረ አውሮፕላን ማረፊያ ስለተነፈገው ወደ አሜሪካ ኒው ጀርሲ ማምራታቸው ተሰምቷል፡፡
የተደራጁት የወንጀለኛ ቡድኖች ጥምረት መሪ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ስልጣን ካልለቀቁ አገሪቱ እልቂት አስከታይ ወደሆነ የእርስ በርስ ጦርነት ታመራለች ሲል ዝቷል ተብሏል፡፡
የሔይቲው ውጥረት አገሪቱን ይበልጥ እያሽመደመዳት እና በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ዜጎችን እያፈናቀለ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ኤሪያል ሔነሪም ወደ አገር ቤት የመመለሻው ነገር የቸገረ ነገር የጠፋ ለመላ እንደሆነባቸው ዘገባው አስታውሷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments