top of page

የካቲት 6 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

  • sheger1021fm
  • Feb 13
  • 2 min read

የአሜሪካው የመከላከያ ሚኒስትር ፒት ሔግሳዝ ዩክሬይንን ከ11 ዓመታት ገደማ በፊት ወደነበረው ድንበሯ መመለሱ የማይሆን ነገር ነው አሉ፡፡


ሩሲያ ከ11 ዓመታት በፊት በዩክሬይን ስር ሲተዳደር የነበረውን የክራይሚያን ልሳነ ምድር ወደ ግዛቷ የቀላቀለችው ታሪካዊ ምክንያቶችን በማንሳት ነበር፡፡


ከዚያም ወዲህ በምስራቅ እና በደቡባዊ ዩክሬይን የሚገኙትን ዳኔስክ፣ ሉሃንስክ፣ ኬርሶን እና ዛፓሮዢያን የሩሲያውያን መኖሪያ እርስቶች ናቸው ብላ በውሳኔ ህዝብ ወደራሷ ቀላቅላቸዋለች፡፡


በነዚህ ግዛቶች የተወሰኑ ስፍራዎች አሁንም ውጊያው መቀጠሉን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


ለዘላቂ እና ሁነኛ ሰላም ሲባል ዩክሬይን አሁን በተጨባጭ ያለው እውነታ ከግምት ማስገባት እንዳለባት የፔንታገኑ አለቃ ተናግረዋል፡፡


የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በምረጡን ቅስቃሳ ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ የዩክሬይኑን ጦርነት በፍጥነት አስቆመዋለሁ ሲሉ መቆየታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡



ሩሲያ እና አሜሪካ የእስረኞች ልውውጥ አደረጉ፡፡


በሁለቱ አገሮች መካከል የእስረኞች ልውውጥ መደረጉን የክሬምሊኑ ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮቭ ማረጋገጣቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡


ሩሲያ የ14 አመታት እስር ተፈርዶበት የነበረውን ማርክ ፎገል የተባለ አሜሪካዊ መልቀቋ ታውቋል፡፡


ዘግይቶ አሜሪካም በስም ያልተጠቀሰ ሩሲያዊ መፍታቷ ተሰምቷል፡፡


የሁለቱ አገሮች የእስረኞች ልውውጥ እንደ መልካም የግንኙነት ማሻሻያ ፍንጭ ተደርጎ እየታየ ነው፡፡


በቀዳሚው የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን የአስተዳደር ዘመን የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እጅግ ከደፈረሰበት ደረጃ ደርሶ ነው፡፡


አዲሱ የአሜሪካ ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ገፅ ለገፅ የመነጋር ፍላጎት ማሳየት ጀምረዋል፡፡



የጋና የቀድሞ የገንዘብ ሚኒስትር ኬን ኦፎሪ አታ በመጠነ ሰፊ ምዝበራ ምክንያት በጥብቅ እየተፈለጉ ነው ተባለ፡፡


ኬን ኦፎሪ አታ በቀድሞው ፕሬዘዳንት ናና አኩፎ አዶ የአስተዳደር ዘመን የገንዘብ ሚኒስትር ነበሩ፡፡


ግለሰቡ ለብክነት በተጋለጠ በሚሊዮኖች ዶላር ለሚቆጠር የመንግስት ገንዘብ በተጠያቂነት ስማቸው በክፉ ሲነሳ መቆየቱን TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡


ተጀምሮ ላልተጠናቀቀ ፕሮጀክት 58 ሚሊዮን ዶላር እንዲከፈል አድርገዋል መባሉ አንዱ ጥፋታቸው ሆኖ እየተነሳ ነው፡፡


አሳማኝነት የጎደለው ወደ 12 ሚሊዮን ዶላር የተጠጋ ገንዘብ ከመንግስት ካዝና ወጪ ሆኖ እንዲከፈል አድርገዋል መባሉ ሌላኛው ነው፡፡


ኬን ኦፎሪ አታ በነዚህና በሌሎች ጥፋቶች ህግ ፊት እንዲቀርቡ በአቃቢያነ ህግ ጥሪ ቀርቦላቸዋል፡፡


በጥሪው መሰረት በፈቃደኝነት የማይቀርቡም ከሆነ አስገዳጅ የመያዣ ትዕዛዝ ይወጣባቸዋል ተብሏል፡፡



የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትናንት ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ ተነጋግረናል አሉ፡፡


ትራምፕ ከፑቲን ጋር በተለይም የዩክሬይኑ ጦርነት በሚቆምበት ጉዳይ በስፋት መነጋገራቸውን በትሩዝ ማህበራዊ ገፃቸው እንዳሰፈሩ አናዶሉ ፅፏል፡፡


ጦርነቱ በሚቆምበትም ሁኔታ በመሰረተ ሀሳብ ደረጃ ተስማምተናል ብለዋል ትራምፕ፡፡


ለዚህም የድርድር ማድረግን በንግግራችን አንስተናል ማለታቸው ተጠቅሷል፡፡


ትራምፕ በአሜሪካ እና በሩሲያ መካከል ቅርርብ እንዲፈጠር ከፑቲን ጋር መግባባታቸው ተናግረዋል፡፡


ከሩሲያው ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር ስለነበራቸው የስልክ ውይይት መንፈስ ለዩክሬይኑ ቮሎድሚር ዜሌንስኪም ማብራሪያ ሰጥቻቸዋሁ ብለዋል፡፡


በዚህ ጉዳይ ከሩሲያ ሹሞች በኩል ያለው አስተያየት በዘገባው አልተጠቀሰም፡፡


የኔነህ ከበደ


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…



📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd


📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s


📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il


留言


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page