በዛሬው ዕለት ሥራ ላይ የሚውለው የአዋሽ አለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ካርድ (Awash International Prepaid card) የባንኩ ደንበኞች በፕላስቲክ ካርዱ አማካይነት እንዲሁም ኤቲኤምን በመጠቀም ገንዘብ ወጪ እንዲያደርጉ ያስችላል ተብሏል።
ከዚህ በተጨማሪም ደንበኞች በፖስ ማሽን ክፍያ እንዲፈጽሙና በኦንላይን ማንኛውንም ዓለም አቀፍ ግብይት በየትኛውም ስፍራ ሆነው መፈጸም እንደሚያስችል የአዋሽ ባንክ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ተወካይ እና የባንኩ ሲኒየር ቺፍ ማርኬቲንግ ኦፊሰር የሆኑት አቶ ዮሐንስ መርጋ አስረድተዋል።
ደንበኞች እንደአስፈላጊነቱ የምንዛሪ ቢሮዎች በመቅረብ በካርዱ ላይ በቂ ገንዘብ ማስሞላት ከመቻላቸውም በተጨማሪ ካርዱ ለአለም አቀፍ ክፍያዎች እና ከጉዞ ጋር ለተያያዙ ወጪዎች ተመራጭ እንደሚያደርገው ተጠቁሟል።
በሌላ በኩል አዋሽ ባንክ የአገልግሎት አድማሱን በማስፋትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ሁሉን አቀፍ የባንክ
አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችለውን የማስተር ካርድ ክፍያ ጌት ዌይ አገልግሎትን(MPGS) በቅርቡ የሚያስተዋውቅ ሲሆን፤ አገልግሎቱ በተለይ በሀገር ውስጥ የሚገኙ የንግዱ ማህበረሰብ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሞባይል መተግበሪያ ወይም ድረ-ገጾችን በመጠቀም የገበያ ትስስርን ለመፍጠር ያስችላቸዋል ተብሏል።
በዓለም ዙሪያ የሚገኙ ደንበኞች የሚፈልጓቸውን ሸቀጦች በኦንላይን ለማዘዝም ሆነ ክፍያ ለመፈጸም እንደሚያግዝ ሲነገር ሰምተናል፡፡
የአዋሽ ባንክ ዓለም አቀፍ የቅድመ ክፍያ ካርድ ከ18 ዓመት በላይ ላሉ መንገደኞች የተዘጋጀ ሲሆን ካርዱን ለማግኘት ፍላጎት ያላቸው ግለሰቦች በቀላሉ እንደ ፓስፖርት፣ ቪዛ እና የበረራ ትኬት ያሉ አስፈላጊ የጉዞ ሰነዶችን ይዘው የምንዛሬ ቢሮ በመገኘት የባንክ አካውንት መክፈት ይጠበቅባቸዋል ተብሏል።
አዋሽ ባንክ ተቀማጩ ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ፣ የሰጠው ብድር ከ172 ቢሊዮን ብር በላይ፣ ጠቅላላ ሀብቱ 260 ቢሊዮን ብር መድረሱን ተናግሯል፡፡
ስራ ከጀመረ 29 ዓመታት የሞላው አዋሽ ባንክ በአሁኑ ሰዓት ከ925 በላይ ቅርንጫፎች፣ ደንበኞቹ ደግሞ 11.5 ሚሊዮን መድረሳቸውን አስረድቷል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Commentaires