top of page

የጥቅምት 7፣2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች


በናይጀርያ በተገለበጠው የነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴ ፍንዳታ ሕይወታቸው ያለፈው ሰዎች ብዛት 153 ደረሰ፡፡


የነዳጅ ማጓጓዣው ቦቴ ተገልብጦ የፈነዳው በአገሪቱ ሰሜናዊ ምዕራብ ግዛት ነው መባሉን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በአደጋው ሕይወታቸውን ካጡት ሌላ በአስራዎች የሚቆጠሩት ደግሞ አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡


የሟቾች እና የተጎጂዎች ብዛት የጨመረው ቦቴው እንደተገለበጠ ሰዎች ነዳጅ ለመቅዳት ወደ ስፍራው በብዛት በመጉረፋቸው ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡


የከፋ ጉዳት የገጠማቸው ስላሉ የሟቾቹ ብዛት ሊጨምር እንደሚችል ተገምቷል፡፡


ተገልብጦ የፈነዳው የነዳጅ ማጓጓዣ ቦቴ ለበርካታ ሰዓታት የዘለቀ ቃጠሎ አስነስቶ እንደነበር በዘገባው ተጠቅሷል፡፡


የኒጀር ወታደራዊ መንግስት በርዕሰ ከተማዋ ኒያሚ በቀድሞው የፈረንሳይ መሪ ቻርልስ ዴ ጉል ስም ተሰይሞ የነበረው መንገድ በሌላ ተካው፡፡


ዴጎል የፈረንሳይ የ2ኛው የአለም ጦርነት ማግስት መሪ ነበሩ፡፡


በፀረ ናዚው ውጊያም ታላቅ ድርሻ ማበርከታቸው ይነገራል፡፡


በኒጀር ኒያሚ በደጎል ተሰይሞ የነበረው መንገድ በወታደራዊ መንግስቱ ጂቦ ባካሪ በሚል እንደተተካ ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ጂቦ ባካሪ የኒጀር የነፃነት ትግል መሪ የነበሩ ግለሰብ ናቸው፡፡


የኒጀር ወታደራዊ መንግስት ከቀድሞዋ የአገሪቱ ቅኝ ገዢ ከፈረንሳይ ጋር ግንኙነቱ በጣሙን እየሻከረ ነው፡፡


የፈረንሳይ ወታደሮችን ከአገሪቱ ካባረረም ቆይቷል፡፡


የኒጀር ወታደራዊ መንግስት የጎዳና ስያሜውን መለወጡ የግንኙነት መሻከሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ይጠቁማል ተብሏል፡፡



ወደ ጋዛ ሰርጥ ትናንት እርዳታ የጫኑ 50 ተሽከርካሪዎች ገቡ ተባለ፡፡


ለሁለት ሳምንታት ወደ ጋዛ አንድም እርዳታ የጫነ ተሽከርካሪ ሳይገባ መቆየቱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡


ወደ ጋዛ 50ዎቹ የእርዳታ ተሽከርካሪዎች የዘለቁት አሜሪካ እስራኤልን በብርቱ ካስጠነቀቀች በኋላ ነው ተብሏል፡፡


አሜሪካ እስራኤል የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦቱን ሁኔታ ካላሻሻለች ለአገሪቱ የምትሰጠውን የጦር እርዳታ እንደምትቀነስ አስጠንቅቃታለች፡፡


ለዚህም የ30 ቀናት የጊዜ ገደብ እንዳስቀመጠችላት ተሰምቷል፡፡


በጋዛ ከዓመት በላይ ሆነው የእስራኤል የጦር ዘመቻ ሰብአዊ ቀውሱን እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡



የኔነህ ከበደ

Comments


bottom of page