የውስጥ ገቢን ለማሳደግ ሲባል በገበሬ እንስሳቶች ላይ ታክስ(ግብር) መጣል መጀመሩን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ተናግሯል፡፡
በአዲሱ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል፤ ‘’የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ሥራ ገቢ ግብር አዋጅ’’ መሰረት የቀንድ ከብቶችን ጨምሮ፣ ፍየል፣ በግ፣ ግመል እና ሌሎች የዳልጋም ሆኑ የጋማ ከብቶች ታክስ እንዲጣልባቸው ይደነግጋል፡፡
ክልሉ በበኩሉ፤ እንስሳቶች ላይ የምጥለው ታክስ(ግብር)፤ ገበሬውን በሚጎዳ መልኩ አይደለም ሲል ተናግሯል፡፡
አዲሱ #አዋጅ ከተያዘው 2017 በጀት ዓመት ጀምሮ ተግባራዊ የሚደረግው ነው ተብሏል፡፡
የተሻሻለው ይህ አዋጅ በቀድሞ አዋጅ ያልነበሩ በርከት ያሉ ህጎችን አካቷል፡፡
ይህም የተደረገው በአርሶ አደሮች መካከል ያለውን ኢ-ፍትሀዊ ግብር አከፋፈልን ለማስተካከል ሲባል እና በሌሎችም ምክንያቶች እንደሆነ በአዋጁ ተጠቅሷል፡፡
ከአዳዲስ ድንጋጌዎች መካከልም በእንስሳቶች ላይ የሚጣል #ግብር አንዱ ሲሆን በክልሉ ያሉ ገበሬዎች ያሏቸውን እንስሳቶች ብዛት አስቆጥረው እያስመዘገቡ ነው፡፡
ይህም በእንዳንዶች ዘንድ ግርታን ፈጥሯል፡፡
ይህ አዲስ ድንጋጌ ምንድነው፤ እንዴትስ ተግባራዊ ይደረጋል?
ሸገር ኤፍ ኤም ራዲዮ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል #ገቢዎች_ቢሮ የትምህርት እና የኮሙኒኬሽን ዳይሮክቶሬት ዳይሬክተር ወ/ሮ ህይወት ከላይ አነጋግሯል፡፡
የስራ ሀላፊዋ፤ ቀድሞ የነበረው አሰራር ለ50 ዓመታት የነበረ እንደሆነ አንስተው ከፌደራል በወረደ ማዕቀፍ መሰረት ከተለያዩ አካላት ጋር በመነጋገር አሰራሩ እንዲሻሻል መደረጉን ተናግረዋል፡፡
በተጨማሪም፤ ከዚህ ቀደም በነበረው የገጠር መሬት ግብር አሰራር መሰረት ገበሬው ለሚጠቀምበት መሬት በተለምዶ ‘’የእንቁላል ዋጋ በመባል የሚከፍለው ከ20 እና ከ30 ብር ያልበለጠ ነበረ፣ አሁን ቢያንስ ያንን የእንቁላል ዋጋ ወደ ዶሮ ዋጋ ከፍ እንዲል ነው የተደረገው ብለውናል፡፡
#በእንስሳት ላይ የሚጣለው ግብር የገበሬውን ኑሮ እና ገቢን ታሳቢ ያደረገ እና ገበሬውን የሚጎዳ አይደለም ሲሉ ዳይሬክተሯ ተናግረዋል፡፡
ገበሬው ከዚህ በፊት በተለያዩ ጊዜያት ይጠየቅ የነበረው የተለያዩ መዋጮዎች እንዳይጠየቅ ከተለያዩ ተቋማት ጋር እንደተነጋገሩም አስረድተዋል፡፡
በተጨማሪም ክልሉ የራሱን ገቢ ራሱ ይቻል እስከተባለ ድረስ፣ የሚታይበትን የበጀት ጉድለት ለመሸፈንና የመንግስት አገልግሎቶችን በተሻለ ሁኔታ ለመስጠት አዋጁ አስፈላጊ እንደሆነ ጠቁመዋል፡፡
እነዚህን መነሾዎች በመገንዘብ፤ ገበሬው አሁን የሚጣልበት ግብር ለመክፈል ዝግጁ አይደለም የሚል እምነት የለንምም ብለዋል፡፡
ቅሬታ ያለው አካልም ካለ በቀበሌና በወረዳ ባሉ ባለሞያዎች በአግባቡ ይስተናገዳል ሲሉም አስረድተዋል፡፡
አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ‘’የገጠር መሬት መጠቀሚያ ክፍያ እና የግብርና ሥራ ገቢ ግብር አዋጅ’’ ማንኛውም የገጠር መሬት የመጠቀም መብት ያለው አርሶ አደር ለምርት ባይጠቀምም በሄክታር ለግብርና የገቢ ግብር 450 ብር መክፈል እንዳለበት ያስረዳል፡፡
ማንያዘዋል ጌታሁን
Comments