ግንቦት 2፣2016 - አቢሲንያ ባንክ የሴቶች ቀን አስመልክቶ ባዘጋጀው የተለያየ ውድድር አሸናፊዎቹን ሸለመ
- sheger1021fm
- May 10, 2024
- 1 min read
አቢሲንያ ባንክ ዓለም አቀፍ የሴቶች ቀን ማርች 8 አስመልክቶ ባዘጋጀው የተለያየ ውድድር አሸናፊዎቹን ሸለመ፡፡
ባንኩ ለ3ተኛ ጊዜ ባዘጋጀው እና ‘’እችላለሁ’’ ሲል በሰየመው መርሐ ግብር በድምፅና በቲክ ቶክ አጭር ቪዲዮ ሰርተው ከ1-3 ደረጃን ላገኙ ሴቶች የገንዘብ ሽልማት መሰጠቱን ተናግሯል፡፡
እንዲሁም በሥራ ፈጠራ ተወዳድረው አሸናፊ ለሆኑ እንስቶች ለሥራ ማስፋፊያ የሚሆን አነስተኛ ወለድ ያለዋስትና ብድር ማመቻቸቱንም ባንኩ ለሸገር በላከው መግለጫ አስረድቷል፡፡

ከየካቲት 29 እስከ መጋቢት 30/2024 ባሉት ቀናት ውስጥ በድምፅ፣ በቲክ ቶክ አጭር ቪዲዮ እና በሥራ ፈጠራ ለመወዳደር ፍላጎቱ ያላቸው ሴቶች የመወዳደሪያ ሥራዎቻቸውን እንዲያቀርቡ የተደረገ ሲሆን፣ በዘርፉ አንቱ በተባሉ ባለሞያዎች እና ከሕዝብ በተሰበሰበ ድምጽ አሸናፊዎች እንዲለዩ ተደርጓል ተብሏል፡፡
በዚሁ የሽልማት መርሐ-ግብር ላይ የሰባት ዓመት ዕድሜ ያላቸውን ሦስት መንታ ሕፃናትን ለውጭ ሀገር የሕክምና ወጪያቸው የሚያግዛቸውን የ ሦስት መቶ ሺህ ብር ባንኩ ድጋፍ ማድረጉንም ጠቅሷል፡፡

ባንኩ ለ3ተኛ ጊዜ የተካሄደውን የ2024 ዘመቻን አካቶ በሥራ ፈጠራ፣ በግጥም፣ በድምፅ እንዲሁም በቲክ ቶክ አጭር ቪዲዮ ተሰጥዖ ያላቸውን ሴቶች አወዳድሮ መሸለሙ፣ ያላቸውን ተሰጥዖ እንዲያጎለብቱና ለሕዝብ በተሻለ እንዲደርሱ መደላድልን ፈጥሯል ተብሏል፡፡
አቢሲንያ ባንክ ከተቋቋመ የ28 ዓመታት ዕድሜን ያስቆጠረ ሲሆን በኃብትና ካፒታል እድገት፣ በአጠቃላይ ገቢ፣ በተቀማጭ ገንዘብ፣ በብድር፣ በትርፍ፣ በቅርንጫፍ ብዛት እና በአስቀማጭ ደንበኞች ቁጥር የላቀ አፈጻጸም እያስመዘገበ አንደሆነ ተናግሯል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio
Website: https://www.shegerfm.com/
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments