top of page

ግንቦት 23፣2016 - የፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ተሻሻለ

  • sheger1021fm
  • May 31, 2024
  • 1 min read

የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባና የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ በአምስት ዓመት ውስጥ ለሁለተኛ ጊዜ ተሻሻለ፡፡


አዋጁ ለሁለተኛ ጊዜ የተሻሻለው ከህጋዊ እና ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ ውጭ የቆዩ የፖለቲካ ቡድኖችን ወደ ህጋዊነት ሲመለሱ በፖለቲካ ፓርቲነታቸው እንዲቀጥሉ የሚያስችል ድንጋጌን ለመጨመር መሆኑን ሰምተናል፡፡


ለሁለት አመት በዘለቀው የሰሜኑ ጦርነት ምክንያት ህውሃት በፓርላማው በሽብርተኝነት ተፈረጆ እንደነበር ይታወሳል፡፡


በዚህም ምክንያት ከህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲነት ተሰርዞ ንብረቱም ተወርሶበት ነበር፡፡


ከፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት በኋላም ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ መመለሱን እንዲሁም ከሽብርተንነት መዝገብ መሰረዙን በመጥቀስ ፓርቲው ህጋዊ ሰውነቴ ይመለስልኝ የሚል ጥያቄ ቢያቀርብም በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኩል ጥያቄው ተቀባይነት ሳያገኝ ቆይቷል፡፡፡

ለዚህም በቦርዱ እንደምክንያት የቀረበው በሽብርተኝነት ተፈርጆ ከፓርቲነት የተሰረዘን የፖለቲካ ፓርቲ ዳግም ህጋዊ አድርጎ ለመመዝገብ ንብረቱንም ለመመለስ የሚያስችል የህግ ማዕቀፍ የለም በሚል ነበር፡፡


ይህን ውዝግብ የሚያስቀር እና ህውሃትንም ወደ ህጋዊ ሰውነቱ ለመመለስ የሚያስችል የማሻሻያ ረቂቅ ህግ ትናንት ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ አግኝቷል፡፡


የሚኒስትሮች ምክር ቤት ለህዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት እንዲላክ በሙሉ ድምፅ የወሰነበት የተሻሻለው የፖለቲካ ፓርቲዎች ምዝገባ የምርጫ ስነ ምግባር አዋጅ ነፍጥ አንግበው ከመንግስትን ጋር ሲዋጉ ከቆዩ በኋላ ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ እንቅስቃሴ የተመለሱትን ህጋዊ የፖለቲካ ፓርቲ አድርጎ ለመመዝገብ የሚያስችል ድንጋጌ የታከለበት ነው ተብሏል፡፡


ከጠቅላይ ሚኒስቴር ፅ/ቤት ያገኘው መረጃ እንደሚሳየው የተጠቀሰውን ጨምሮ በአራት የተለያዩ የአዋጅ ማሻሻያዎች ላይ ተወያይቶ ለፓርላማው እንዲላኩ ውሳኔ አሳልፏል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Comments


Sheger App Logo
iOS Store
Google Play

    ሸገር
102.1

ሸገር ኤፍ ኤም 102.1 አዲስ የሬዲዮ አቀራረብ መላና አዲስ ቃና ይዞ የቀረበ በሀገሪቱ የሚዲያ ገበያ ላይ መሪ ሚና የሚጫወት ጣቢያ ነው፡፡

ሁሌም ከሸገር ጋር ሁኑ
ሸገር የእናንተ ነው
ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር! 

Sheger Radio | Sheger 102.1FM  © 2025 Adey Tensae Media & Entertainment PLC.  

bottom of page