top of page

ግንቦት 7፣2016 - የባህር ማዶ ወሬዎች


ባለፉት ጥቂት ቀናት በጋዛ ሰርጥ ደቡባዊ ጠርዝ ከምትገኘው ራፋ ከተማ እና ከሰሜናዊ የሰርጡ ክፍል ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ፍልስጤማውያን መፈናቀላቸውን የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እወቁልኝ አለ፡፡


እስራኤል በራፋ መጠነ ሰፊ የጦር ዘመቻ የጀመረችው በቅርቡ ነው፡፡


መጠነ ሰፊው ዘመቻ ከመከፈቱ አስቀድሞ የእስራኤል ጦር በብዙ ሺህዎች የሚቆጠሩ ፍልስጤማውያን ከከተማዋ ለቅቀው እንዲወጡ ቀጭን ትዕዛዝ ሰጥቷቸዋል፡፡


ራፋ በቀደሙት ወራት ከተለያዩ የጋዛ አካባቢዎች በጦርነት የተፈናቀሉ ፍልስጤማውያን መጠለያ ሆና መቆየቷን አሶሼትድ ፕሬስ አስታውሷል፡፡


በራፋ የሚካሄድ የጦር ዘመቻ የጋዛውን ሰብአዊ ቀውስ በእጅጉ እንደሚያባብሰው ከእስራኤል አጋሮች ሳይቀር የስጋት ድምፆች እያስተጋቡ ነው፡፡


በዚያ ላይ የእስራኤል ጦር በጋዛ ሰሜናዊ ክፍል ጃባልያ የስደተኞች ሰፈር አዲስ ዘመቻ መክፈቱ ተሰምቷል፡፡



የፈረንሳይ ፖሊሶች በከባድ ወንጀለኞች ማደን ተግባር ተጠምደዋል ተባለ፡፡


ትናንት በሰሜናዊ ፈረንሳይ በቅፅ ስሙ ዝንቡ የተባለውን የአደገኛ እፅ አስተላላፊ የተደራጀ የወንጀል ቡድን መሪን ወደ እስር ቤት ሲያጓጉዝ በነበረ ሽፋን መኪና ላይ በተከፈተ ጥቃት ሁለት ጠባቂዎች መገደላቸው አገሪቱን አስደንግጧል፡፡


ሌሎች 3 ጠባቂዎች ደግሞ ከፍተኛ አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ዘ ኢንዲፔንደንተት ፅፏል፡፡


ጭምብል ያደረጉት ሁለት ጥቃት አድራሾች ጥቃቱን ከፈፀሙ በኋላ አደገኛውን ወንጀለኛ አስመልጠው ይዘው መጥፋታቸው ተሰምቷል፡፡


ፕሬዘዳንት ኢማኑኤል ማክሮን አስፈላጊው ሁሉ ተደርጎ ወንጀለኞቹ እንዲያዙ ማዘዛቸው ተሰምቷል፡፡


ፖሊሶች በሰሜናዊ ፈረንሳይ በበርካታ ስፍራዎች ኬላዎችን አቁመው ጥቃት አድራሾቹን እና አምላጩን እስረኛ በማደን ላይ ናቸው ተብሏል፡፡


አሰሳው 2ኛ ቀኑን አስቆጥራል፡፡


ወንጀለኞቹ ሲጓጓዙባቸው ከነበሩት ተሽከርካሪዎች አንዷ ተቃጥላ እንደተገኘች በዘገባው ተጠቅሷል፡፡



ግብፅ እና እስራኤል በራፋ መተላለፊያ ኬላ መዘጋት ሰብአዊ እርዳታ በመስተጓጎሉ በአንቺ ነሽ ፤ አንቺ ነሽ እየተከሰሱ ነው፡፡


እስራኤል እርዳታ የጫኑ ተሽከርካሪዎች እንዳያልፉ የከለከለችው ግብፅ ነች ማለቷን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


ግብፅ በፊናዋ በስፍራው የእስራኤል ጦር የሚያካሂደው ዘመቻ እንጂ እኔ በጭራሽ ሰብአዊ እርዳታ የጫኑ መኪኖች እንዳያልፉ አልከለከልኩም እያለች መሆኑ ተሰምቷል፡፡


እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከጀመረች ከ7 ወራት በላይ ሆኗታል፡፡


በጋዛ ሰብአዊ ቀውሱ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡


እስራኤል የራፋ ዘመቻዋን መጀመሯ ሰብአዊ ቀውሱን በእጅጉ ሊያከፋው ይችላል የሚለው የስጋት ድምፅ እየጎላ ነው፡፡



በዩጋንዳ በወንዞች በሐይቆች እና በሌሎች የውሃ አካላት አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ከጎርፍ እና ከውሃ ሙላት እንዲጠበቁ ማስጠንቀቂያ ተሰጣቸው፡፡


በአሁኑ ወቅት እንደ ቪክቶሪያ ሐይቅ ያሉ የውሃ አካላት ከአፍ እስከ ገደፋቸው እየሞሉ መሆኑን ዘ ኢስት አፍሪካን ፅፏል፡፡


በአገሪቱ የሚጥለው ዶፍ ዝናብ ለወንዞች እና ለሀይቆች ጢም ብሎ መሙላት ዋነኛው ምክንያት ነው ተብሏል፡፡


በዚህም የተነሳ የውሃ እና የአካባቢ ሚኒስትሩ ሳም ቺፕቶሪስ በውሃ አካላት አቅራቢያ የሚኖሩ ዜጎች ከጎርፍ እና ከውሃ ሙላት እንዲጠበቁ ማስጠንቀቂያ መስጠታቸው ተሰምቷል፡፡


ኬኒያ፣ ታንዛኒያ፣ ሩዋንዳ፣ እና ቡሩንዲ በከፍተኛ ጎርፍ ሲፈተኑ መሰንበታቸውን ዘገባው አስታውሷል፡፡


የኔነህ ከበደ



የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…


Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw


Youtube: http://tiny.cc/ShegerFM1021Radio


Website: https://www.shegerfm.com/


Commenti


bottom of page