የአሜሪካ 47ኛው ፕሬዘዳንት በመሆን ዛሬ በዓለ ሲመታቸውን የሚያከናውኑት ዶናልድ ትራምፕ በርካታ ትዕዛዛትን እንደሚሰጡ እወቁልኝ አሉ፡፡
ትራምፕ በዛሬው እለት በርካታ ትዕዛዛትን በመፈረም ስራ ላይ ይዋሉ ለማለት መሰናዳታቸው እወቁለኝ ያሉት ትናንት በዋሽንግተን ዲሲ ከደጋፊዎቻቸው ጋር ባካሄዱት ቅድመ በዓለ ሲመት የድል ስብሰባ ወቅት እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
ከትራምፕ ትዕዛዛት መካከል ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአሜሪካ ጠራርጎ ማባረሪያው በቀዳሚነት ተጠቅሷል፡፡
የማይረቡ ያሏቸውን የተሰናባቹን ፕሬዘዳንት ጆ ባይደንን ትዕዛዛት እንደሚሽሯቸው ትራምፕ ለደጋፊዎቻቸው ተናግረዋል፡፡
መገናኛ ብዙሃን ትራምፕ በዛሬው እለት ከ200 ያላነሱ አዳዲስ ትዕዛዛትን እንደሚፈርሙ በስፋት እየዘገቡ መሆኑን መረጃው አስታውሷል፡፡
የጋዛው የተኩስ አቁም ትናንት ከሰዓታት መዘግየት በኋላ ስራ ላይ መዋል ጀመረ፡፡
በስምምነቱ መሰረት ሐማስ ሶስት ሴት ታጋቾን እንደለቀቀ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
እስራኤል በፊናዋ 90 ፍልስጤማውያን እስረኞችን መፍታቷ ታውቋል፡፡
ከእስራኤል እስር ቤቶች የተለቀቁት እስረኞች አብዛኞቹ ሴቶች እና ሕፃናት ናቸው ተብሏል፡፡
የተፈቱት እስረኞች በዌስት ባንክ የፈንጠዝያ አቀባበል እንደተደረገላቸው ተጠቅሷል፡፡
በሐማስ የተለቀቁት ታጋቾች ደግሞ በቴል አቪቭ ሆስፒታል የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑ ታውቋል፡፡
የእስራኤሉ የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ኢታማር ቤን ግቪር ስልጣናቸውን በፈቃዳቸው ለቀቁ፡፡
ቤን ግቪር ስልጣናቸው የለቀቁት ከሐማስ ጋር የተደረሰውን የተኩስ አቁም ስምምነት በመቃወም እንደሆነ አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
በስም እና በሀላፊነታቸው ባይጠቀሱም ሁለት ሌሎች ሚኒስትሮችም መልቀቃቸውን የፖለቲካ ማህበራቸው እወቁልኝ ብሏል፡፡
ሶስቱ ሚኒስትሮች መልቀቃቸው የጥምር መንግስቱን መፍረስ እንደማያስከትል ተጠቅሷል፡፡
ቤን ግቪር የጋዛው የተኩስ አቁም ስምምነት ለሐማስ እጅ ከመስጠት ይቆጠራል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
የብሔራዊ ደህንነት ሚኒስትር ሆነው የቆዩት ኢታማር ቤን ግቪር በእስራኤል እጅግ የከረረ የፖለቲካ አቋም ከሚያራምዱት አንዱ ሆነው እንደሚነሱ መረጃው አስታውሷል፡፡
የየመን ሁቲ ታጣቂዎች አንዳች ጥቃት የሚደርስብን ከሆነ ምላሻችን የከፋ ይሆናል አሉ፡፡
ሁቲዎቹ ትናንት ወደ በአሜሪካ የአውሮፕላን ተሸካሚ የጦር መርከብ ላይ ጥቃት ሰንዝረዋል መባሉን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡
ቀደም ሲልም እስራኤል የጋዛ የጦር ዘመቻዋን እንድታቆም ለማስገደድ አልመው የድሮን እና የሚሳየል ጥቃት ሲሰነዝሩባት ቆይተዋል፡፡
የጋዛው የተኩስ አቁም ከትናንት አንስቶ ስራ ላይ መዋል ጀምሯል፡፡
ይሄም ሆኖ ሁቲዎቹ በጠላቶቻችን አንዳች ጥቃት ከተፈፀመብን ምላሽ ከመስጠት ወደ ኋላ አንልም ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
እስራኤል የጋዛውን የተኩስ አቁም ከጣሰች አንለቃትም ሲሉ ዝተዋል ሁቲዎቹ፡፡
ርዕሰ ከተማዋ ሰንዓን ጨምሮ የሰሜናዊ የመንን ክፍል የሚያስተዳድሩት ሁቲዎቹ የኢራን ሁነኛ የጦር እና የፖለቲካ ሸሪኮች መሆናቸው ይነገራል፡፡
ኬንያ ከ200 በላይ ተጨማሪ የፖሊስ ባልደረቦችን ወደ ሔይቲ ላከች፡፡
ምስራቅ አፍሪካዊቱ አገር ከአመት በፊት ወደ ሔይቲ 400 ፖሊሶቿን እንደላከች TRT አፍሪካ አስታውሷል፡፡
የካሪቢያኗ አገር ሔይቲ በተደራጁ የወሮበሎች ቡድኖች ሥርዓተ አልበኝነት ከነገሰባት ቆይታለች፡፡
ሌሎች 10 አገሮችም ከ3 ሺህ በላይ ፖሊሶቻቸውን ወደ ሔይቲ ለመላክ ቀደም ብለው ቃል ቢገቡም እስካሁን ግን አላሳኩትም ተብሏል፡፡
ሔይቲ አሁንም በተደራጁት የወሮበሎች ቡድኖች አበሳዋን እያየች ነው፡፡
በአሃዝ ተለይቶ ባይጠቀስም ጓቴማላ፣ ኤልሳልቫዶር ፣ ጃማይካ እና ብራዚል ወደ ሔይቲ የፖሊስ መኮንኖቻቸውን ልከዋል ተብሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
📌 Website: https://shorturl.at/yCz7q
📌 YouTube: https://tinyurl.com/ky57kspd
📌 WhatsApp: https://tinyurl.com/ycxjmm3s
📌 Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
📌 Linkedin : https://tinyurl.com/yhycs5rs
Commentaires