top of page

ጥር 15 2017 - የባህር ማዶ ወሬዎች

 

በአሜሪካ ከሎስአንጀለስ በተስተሰሜን አዲስ የሰደድ እሳት ተቀሰቀሰ፡፡

 

አዲሱ የሰደድ እሳት ካስታይቅ አካባቢ የሚገኙ ኮረብታማ ስፍራዎችን እያዳረሰ መሆኑን አረብ ኒውስ ፅፏል፡፡

 

የሰደድ እሳቱ በጥቂት ሰዓታት በአሁኑ ወቅት 5 ሺህ ሔክታር ስፍራ መሸፈኑ ታውቋል፡፡

 

ደረቅ እና ከበድ ያለው ነፋስ ለሰደድ እሳቱ መንቀልቀል በምክንያትነት ቀርቧል፡፡

 

በ10 ሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች የሰደድ እሳቱ ከሚያሰጋቸው ስፍራዎች ለቅቀው እንዲወጡ ታዘዋል፡፡

 

ከ31 ሺህ የማያንሱ ሰዎች የለቃችሁ ውጡ ትዕዛዙ ይመለከታቸዋል ተብሏል፡፡

 

4 ሺህ 600 እስረኞችም ወደ ሌላ ስር ቤት እንዲዛወሩ መደረጉ ታውቋል፡፡


 

የኬንያ መንግስት ወደ አገሪቱ ለሚመጡ አፍሪካውያን መግቢያውን አቀለለላቸው ተባለ፡፡

 

ቀደም ሲል ወደ አገሪቱ የሚገቡ አፍሪካውያን አስቀድመው የኤሌክትሮኒክሳዊ የጉዞ ማረጋገጫቸው ማሟላት እንዳለባቸው የሚጠይቅ መላ ስራ ላይ ውሎ እንደነበር ቢቢሲ አስታውሷል፡፡

 

ሆኖም ይሄን ማሟላቱ ከውስብስብ የቪዛ ስርዓት የባሰ ነው በሚል ሲተች መቆየቱ ተጠቅሷል፡፡

 

በአዲሱ አሰራር ግን አፍሪካውያን በቅድሚያ ማረጋገጫውን ማቅረብ ሳያስፈልጋቸው በአገሪቱ ጉብኝት ማድረግ ይችላሉ ተብሏል፡፡

 

አዲሱ አሰራር ከሶማሊያ እና ሊቢያ በስተቀር ለሁሉም የአፍሪካ አገሮች መፈቀዱ ታውቋል፡፡

 

በአሁኑ ወቅት በርካታ የአፍሪካ አገሮች የጉዞ መመዘኛቸውን እያቀለሉት መምጣታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

በታንዛኒያ ተዋቂው ፖለቲከኛ ቱንዱ ሊሱ የዋነኛው ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር (ቻዴማ) መሪ ሆነው ተመረጡ፡፡

 

ቱንዱ ሊሱ የፖለቲካ ማህበር መሪነቱን ከፍሪማን ምቦዌ እንደተረከቡ ዘ ሲትዝን ፅፏል፡፡

 

ለፖለቲካ ማህበሩ መሪነት የጦፈ ፉክክር መደረጉ ታውቋል፡፡

 

ፋሪማን ምቦዌ ዋነኛውን ተቃዋሚ የፖለቲካ ማህበር ቻዴማን ለ21 አመታት መምራታቸውን መረጃው አስታውሷል፡፡

 

የእነቱንዱ ሊሱ ወገኖች ምቦዌ በገዢ የፖለቲካ ማህበር CCM አንፃር መለሳለስ እያሳዩ ነው በሚል ውስጣዊ ነቀፋ አበርትቶውባቸው ነበር ተብሏል፡፡

 

አሁን የቻዴማ መሪ የሆኑት ቱንዱ ሊሱ ቀደም ሲል የፖለቲካ ማህበሩ ምክትል ሊቀመንበር እንደነበሩ መረጃው አስታውሷል፡፡

 

 

ማሊ ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በቀጠናው ፅንፈኞችን ለመዋጋት ጥምር ሀይል ለማሰማራት መሰናዳታቸውን የኒጀሩ የመከላከያ ሚኒስትር ተናገሩ፡፡

 

አገሮቹ በጥምረት 5 ሺህ ወታደሮችን እንደሚያሰልፉ የኒጀሩ የመከላከያ ሚኒስትር ጄኔራል ሳሊፉ ሞዲ መናገራቸውን አናዶሉ ፅፏል፡፡

 

በጥምር የሚሰማራው ሰራዊት ከፅንፈኞች ጋር ከመዋጋት በተጨማሪ ድንበር ዘለል የተደራጀ ወንጀልንም የመከላከል ዓላማ አለው ተብሏል፡፡

 

3ቱ አገሮች የሚገኙበት የሳሕል ቀጠና የፅንፈኛ ታጣቂዎች ተፅዕኖ ያየለበት መሆኑ ይነገራል፡፡

 

ማሊ ፣ ኒጀር እና ቡርኪናፋሶ በግልበጣ የመንግስት ስልጣን በተቆጣጠሩ ወታደራዊ አስተዳደሮች የሚመሩ አገሮች ናቸው፡፡

 

አዲሱ ጥምር ጦራቸው ተልዕኮውን በአግባቡ ለመወጣት የአየር እና የወታደራዊ ደህንነት ድጋፍ እንደሚኖረውም ታውቋል፡፡

 

 

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ህገ-ወጥ እና ሰነድ አልባ ስደተኞችን የሚከላከሉ ተጨማሪ 1 ሺህ 500 ወታደሮች በደቡባዊው ድንበር እንዲሰማሩ አዘዙ፡፡

 

ወታደሮቹ ስደተኞች ወደ አሜሪካ እንዳያልፉ ማገጃ ኬላዎችን የማቆም ተልዕኮ ተሰጥቷቸዋል መባሉን CBS ፅፏል፡፡

 

ሌሎችንም የድንበር ጥበቃ ተግባራትን ያከናውናሉ ተብሏል፡፡

 

ወታደሮቹ በድጋፍ ሰጭ አውሮፕላኖችም እንደሚታገዙ ታውቋል፡፡

 

በአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መስሪያ ቤት አማካይነት ሲከናወን የቆየ የጥገኝነት ፈላጊዎች ቅበላ እንዲቆም መደረጉ ተሰምቷል፡፡

 

ግለሰብ ዜጎች እና ምግባረ ሰናዮች ጥገኝነት ፈላጊዎችን የሚያስተናግዱበት አሰራር እንዲቆም መደረጉ ታውቋል፡፡

 

ዶናልድ ትራምፕ በምረጡኝ ዘመቻ ላይ ከነበሩበት ጊዜ አንስቶ ሰነድ አልባ ስደተኞችን ከአገሪቱ ጠራርጌ አባርራለሁ ሲሉ ቆይተዋል፡፡

 

የጥገኝነት ጥያቄያቸው ሲታይ የቆየ ስደተኞችም ጉዳይ ሂደት እንዲቆም ተዳርጓል ተብሏል፡፡

 

የኔነህ ከበደ

 

Комментарии


bottom of page