top of page

ጥር 2፣2017 - በግሉ የህክምና ዘርፍ የሚቋቋሙ ማዕከላት ኢትዮጵያን ለህክምና የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የሚያግዝ ነው ተባለ

በግሉ የህክምና ዘርፍ የሚቋቋሙ አዳዲስ ማዕከላት ኢትዮጵያንም በውጭ ሀገር ህክምና የምታጣውን የውጭ ምንዛሪ ለማስቀረት የሚያግዝ ነው ተባለ፡፡


በማህፀንና ጽንስ እንዲሁም በህፃናት ህክምና ላይ በተሰማሩ ባለሞያዎች የተቋቋመው ‘’ታይም የእናቶች ህፃናት ጤና እና የቀዶ ህክምና ማዕከል’’ ወደ ስራ መግባቱ ተነግሯል፡፡


በባለሞያዎቹ በጋራ የተመሠረተው የህክምና ማዕከል በኢትዮጵያ ጥቂት ባለሞያዎች ያሉትንና ለላቀ ህክምና የውጭ ሀገር ጉዞ የሚጠይቁ አገልግሎቶችን እዚሁ ለመስጠት የሚያስችል ነው ተብሏል፡፡


በተለይ በእናቶችና ህፃናት ጤና ላይ የሚሰጡ የህክምና አገልግሎቶች ከዚህ ቀደም የሚታዩ ክፍተቶችን በመለየት በተሻለ መልኩ ለማገልገል በዘርፉ ባለሞያዎች ማዕከሉ መመስረቱን የሚናገሩት ከማዕከሉ መስራቾች አንዱና ዋና ስራ አስፈፃሚ የሆኑት ዶክተር አታክልቲ ጸጋይ ናቸው፡፡

የእናቶችና የህፃናት ጤና እጅግ ቅድሚያ ከሚሰጣቸው ጉዳዮችና የአንድ ሀገር የጤና ተቋም እንደመስፈርት ከሚወሰድባቸው አገልግሎቶች ዋነኛው ነው ብለዋል፡፡


የህክምና ማዕከሉ ብዙሃኑን የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ለማድረግ የተቋቋመ መሆኑንም ዶክተር አታክልት የተናግረዋል፡፡


ማህበራዊ ሀላፊነትን ለመወጣትም በማዕከሉ ዘወትር እሁድ ለህፃናት ነፃ የህክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ የተናገሩት ደግሞ የሆስፒታሉ የህፃናት ስፔሻሊስት ሃኪም የሆኑት ዶክተር በላቸው ፍርዱ ናቸው፡፡


ወደፊትም ነፃ የህክምና ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት ወይም በሌላ ቦታ የሚገኙ ህፃናትን እየሄድን በመጎብኘት ለማከምና ለመደገፍ እቅድ አለን ብለዋል፡፡


ኢትዮጵያ በሜዲካል ቱሪዝም ዘርፍ ብዙ አልተጠቀመችበትም የሚሉት ከተቋሙ መስራቾች አንዱና የሊያና ዲጂታል ሄልዝ ዳይሬክተር ዶክተር ግርማ አባቢ ወደ ውጭ ሀገራት የሚደረግ የህክምና ጉዞውን በማስቀረት የሀገር ቤት የህክምና አገልግሎት ጥራቱን ማሻሻል ላይ በማተኮር እንሰራለን ብለዋል፡፡


ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የጤና ሥርዓት በግልም ዘርፍ የሚታማበት ነገር እንዳለ እናውቃለን ያሉት ዶ/ር ግርማ ስለዚህ ይሄንን በደንብ ታሳቢ በማድረግ ሊለውጥ የሚችል አሰራር መዘርጋቱን ተናግረዋል፡፡


በመጪው እሁድ 4 ቀን 2017 ዓ.ም የሚመረቀው ታይም የናቶች ህጻናትና የቀዶ ህክምና ማዕከል 85 ሚሊዮን ብር ወጪ እንደተደረገበት ሰምተናል፡፡


ማዕከሉ ወደ ስራ መግባቱን አስመልክቶም ለአንድ ሳምንት ያህል ለእናቶችና ህፃናት ነፃ የህክምና አገልግሎት ማሰናዳቱን ተናግሯል፡፡


ምህረት ስዩም

Comments


bottom of page