በዌስት ባንክ ጄኒን ከተማ ወደሚገኝ ሆስፒታል የህክምና ባለሞያዎች ተመስለው የገቡ የእስራኤል ኮማንዶዎች ሶስት ተኝቶ ታካሚ ፍልስጤማውያን መግደላቸው ተሰማ፡፡
ወደ ሆስፒታሉ በመዝለቅ የድምፅ መከላከያ በተገጠመላቸው የጦር መሳሪያዎች ግድያው ፈፅመዋል የተባሉት 10 የእስራኤል ልዩ ሀይል ወታደሮች እንደሆኑ ቲአርቲ ዎርልድ ፅፏል፡፡
የእስራኤል ጦር የተገደሉት ፍልስጤማውያን ጥቃት ለማድረስ ሲያደባ ነበር የተባለ ታጣቂ ቡድን አባሎች ናቸው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የጀኒን ከተማ ፍልስጤማውያን ነዋሪዎች ሆስፒታል ውስጥ የተፈፀመውን ግድያ ለመቃወም ሰልፍ ተጠርተዋል ተብሏል፡፡
እንደ ጋዛ ሰርጥ ባይሆንም በዌስት ባንክም የጋዛው ጦርነት ከተቀሰቀሰ ወዲህ ከ380 የማያንሱ ፍልስጤማውያን በእስራኤል ወታደሮች መገደላቸው ይነገራል፡፡
የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ሰሞኑን በዮርዳኖስ በሚገኝ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ላይ በተሰነዘረ የድሮን ጥቃት ሶስት የአሜሪካ ወታደሮችን በገደሉት የኢራቅ ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድባቸው አዝዣለሁ አሉ፡፡
በእሁድ ሌሊቱ ጥቃት ከተገደሉት ሌላ 30 ያህሉ የአሜሪካ ወታደሮች አካላዊ ጉዳት ገጥሟቸዋል ተብሏል፡፡
ቀደም ሲል ፕሬዘዳንት ባይደን ጥቃት አድራሾቹ አፍቃሪ ኢራን ታጣቂዎች እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
የኢራቅ ተከላካይ የተሰኘ ታጣቂ ቡድን ለጥቃቱ ሀላፊው እኔ ነኝ ማለቱን ቢቢሲ አስታውሷል፡፡
ፕሬዘዳንት ባይደን ያን ያህል ቀጠናዊ ባይሆንም በጥቃት አድራሾቹ ላይ ያነጣጠረ ውሱን እርምጃ ይወሰዳል ማለታቸው ተሰምቷል፡፡
ጥቃት አድራሾቹ የኢራን ሽርካዎች ናቸው ቢባልም ቴሕራን ግን ፈጥና በዚህ ጥቃት እጄ የለበትም ብላለች፡፡
በኢራቅ፣ ሶሪያ እና በአቅራቢያው አገሮች በሚገኙ የአሜሪካ የጦር ይዞታዎች ላይ በድሮን እና ሮኬት የሚፈፀመው ጥቃት እየተበራከተ መምጣቱ ይነገራል፡፡
በቀኝ አክራሪነታቸው የሚታወቁት የእስራኤል የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትር ከሐማስ ጋር ሊደረስ ይችላል በተባለው የተኩስ አቁም ጉዳይ የእስራኤል መንግስት ሊፈርስ ይችላል ሲሉ አስጠነቀቁ፡፡
የአገር ውስጥ ደህንነት ሚኒስትሩ ኢትማር ቤን ግቪር ከሐማስ ጋር የተኩስ አቁም ስምምነት ተደረሰ ማለት የእስራኤል መንግስት እንደፈረሰ ቁጠሩት ማለታቸውን TRT ዎርልድ ፅፏል፡፡
የእስራኤል የጦር ወቅት ካቢኔ የተመሰረተው ክኔሴት በተሰኘው የእስራኤል ፓርላማ 64 መቀመጫዎች ባሉት የፖለቲካ ጥምረት ነው፡፡
ፓርላማው በአጠቃላይ 120 መቀመጫዎች አሉት፡፡
ከሐማስ ጋር የሚደረሰውን ስምምነት በመቃወም የተወሰኑ የፖለቲካ ማህበራት ከጥምረቱ ከወጡ እስራኤል ወደ አጣዳፊ ምርጫ እንድትገባ ሊያስገድዳት ይችላል፡፡
የፍልስጤማውያኑ የጦር ድርጅት (ሐማስ) የቀረበልኝን የተኩስ አቁም ሀሳብ እየመረመርኩ ነው ማለቱ ተሰምቷል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments