የጸደቀው የንብረት ማስመለስ አዋጅ ተፈጻሚ ሲሆን ምክንያታዊ ያልሆኑ ክሶች እንዳይመጡ ተጠርጣሪው ግለሰብ ስለ ጉዳዩ ቀርቦ እንዲያስረዳ ዕድል የሚሰጥና በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ብቻ ተፈጻሚ የሚሆን ነው ተባለ።
አዋጁን እንዲያስፈጽም ኃላፊነት የተሰጠው የፍትህ ሚኒስቴር ጥር 1 የጸደቀውን የንብረት ማስመለስ አዋጅ በተመለከተ ዛሬ ለጋዜጠኞች ማብራሪያ ሰጥቷል።
አዋጁ በህገ-ወጥ መንገድ በወንጀል የተገኘ ንብረትን በአግባቡ በማስመለስ የሀገርንና የህዝብን ሀብት ከወንጀል ለመጠበቅ የሚሰራበት ነው ተብሏል።
ማራሪያውን የሰጡት የፍትህ ሚኒስትሯ ሃና አርአያስላሴ የንብረት ማስመለስ አዋጁን እንዲያስፈጽም ኃላፊነቱ የተሰጠው ለፍትህ ሚኒስቴር ቢሆንም በዘፈቀደ የሚተገበር ሳይሆን በፍርድቤት ውሳኔ ላይ ብቻ ተመርኩዞ የሚፈጸም ነው ብለዋል።
ነገር ግን የማይመለስ ጉዳት ማለትም ንብረቱ ከሃገር ሊሸሽና ሌሎች ተመሳሳይ ጉዳት ደርሶ ከሆነ ጊዜያዊ እግድ በራሱ በፍትህ ሚኒስቴር ያለፍርድቤት ትዕዛዝ እንደሚሰጥ ሚኒስትሯ ተናግረዋል።
አንድ ግለሰብ በቅን ልቦና ባለማወቅ ንብረቱ ህገ-ወጥ መሆኑን ሳያውቅ የገዛ ቢሆን ንብረቱ እንዳይወረስ ተገቢውን ጥበቃ የሚሰጥ ነው ተብሏል።
በአዋጁ ላይ በተደነገገው መሰረትም ህገ-ወጥ ንብረት በማፍራት የተጠረጠረ ሰው ያለደረሰኝ በሰውም ሆነ ሌሎች ያስረዱልኛል ባላቸው ማስረጃዎች ጥፋተኛ አለመሆኑን ማስረዳት የሚያስችል መመሪያ እንዳለውም ሚኒስትሯ ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም አዋጁን ለማስፈጸም ከተለያዩ ሀገራት ጋር በትብብር የሚሰራበት መሆኑን የጠቀሱት ሚኒስትሯ ንብረቱ ኢትዮጵያ ቢሆንም በውጭ ሀገራት በህገ-ወጥ መንገድ የተገኘ መሆኑ ከተረጋገጠ ለማስመለስ የሚሰራበት ነው ተብሏል።
ሌላው በጥፋተኝነት ላይ ያልተመሰረተ የንብረት ማስመለስ አዋጁ ያካትታል የተባለ ሲሆን ይህም ተጠርጣሪው በሞት ቢለይ ወይም ከሀገር የሸሸ ቢሆን ንብረቱ እንዲሁ የሚቀር ሳይሆን እንዲታገድና ጉዳዩ ተጣርቶ ግለሰቡ በሌለበት እንዲወረስ ይደረጋል ተብሏል።
በአጠቃላይ የንብረት ማስመለስ አዋጁ ዋና አላማ በህገ-ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ የኢኮኖሚ ወንጀል በመፈጸም በንብረት በመሸፈን ጉዳት ያደረሱትን በመከላከል ህጋዊና ደክመው ንብረት ያፈሩ ዜጎችን ለመጠበቅ እንደሆነ የፍትህ ሚኒስቴር ተናግሯል።
ምህረት ስዩም
ቴሌግራም: https://t.me/ShegerFMRadio102_1
ዌብሳይት: https://shorturl.at/yCz7q
Comments