የአሜሪካ መንግስት በሱዳን ከቀጠለው ጦርነት ጋር ግንኙነት አላቸው ባላቸው ሶስት የሱዳን ኩባንያዎች ላይ ማዕቀብ መጣሉ ተሰማ፡፡
ማዕቀቡ ከተጣለባቸው ኩባንያዎች ሁለቱ RSF ከተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጋር የተቆራኙ እንደሆኑ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
3ኛው ከሱዳን መንግስት ጋር ተያያዥነት ያለው ነው ተብሏል፡፡
ሶስቱ ኩባንያዎች ለማዕቀብ የተዳረጉት የሚያፈሩትን ገንዘብ ለጦርነቱ መደገፊያ ያውላሉ ተብለው መሆኑ ታውቋል፡፡
የሱዳን መንግስት ጦር እና RSF የተሰኘው ፈጥኖ ደራሽ ሀይል ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ ከ9 ወራት በላይ ሆኗቸዋል፡፡
በጦርነቱ ከ12 ሺህ በላይ ሰዎች ሲገደሉ ከ7 ሚሊዮን የማያንሱት ለስደት እና መፈናቀል መዳረጋቸው ይነገራል፡፡
የፍልስጤም አስተዳደር በጋዛ ሰርጥ ተገድለው በድናቸው በጅምላ ተቀብሮ የተገኘ የ30 ፍልስጤማውያን ጉዳይ በአለም አቀፍ ደረጃ ይመርመርልኝ ሲል ጥያቄ አቀረበ፡፡
የ30ዎቹ ሰዎች አስከሬን በጥቁር ፕላስቲክ ውስጥ ተከትቶ በጅምላ ተቀብረው መገኘታቸውን አልጀዚራ ፅፏል፡፡
አስከሬናቸው ሲገኝ ዓይናቸው በጨርቅ ተሸፍኖ እና እጃቸውም የፊጥኝ ታስሮ ነበር ተብሏል፡፡
የፍልስጤም አስተዳደር በሰዎቹ ላይ የግፍ ግድያውን የፈፀመው የእስራኤል ጦር ነው ሲል መክሰሱ ተሰምቷል፡፡
የፍልስጤም አስተዳደር ጉዳዩ በአለም አቀፍ ደረጃ እንዲመረመርለት ጠይቋል፡፡
በዚህ ጉዳይ የእስራኤል መንግስት አስተያየት አልተጠቀሰም፡፡
የእስራኤል ጦር የጋዛ የጦር ዘመቻዬ በሐማስ ላይ ያነጣጠረ ነው ባይ ነው፡፡
አሜሪካ በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የኢራን ደጋፊ ታጣቂዎችን መደብደቧ አይቀሬ እንደሆነ ጉዳዩን በቅርበት የሚያውቁ ሹሞች ተናገሩ ተባለ፡፡
በኢራቅ እና ሶሪያ የሚገኙ የኢራን ደጋፊ ታጣቂ ቡድኖች በአሜሪካ የጦር እርምጃ የመመታታቸው ነገር ያለቀ የደቀቀ ጉዳይ እንደሆነ በስም ካልተጠቀሱ ሹሞች ሰምቻለሁ ያለው CBS አውርቷል፡፡
ሹሞቹ ድብደባው ለቀናት እንደሚጥልም ፍንጭ ሰጥተዋል ተብሏል፡፡
አሜሪካ በኢራን ደጋፊ ታጣቂዎች ላይ የጦር እርምጃውን የምትወስደው በዮርዳኖስ ወሰን በሚገኝ የጦር ሰፈሯ ላይ ሰሞኑን ለተሰነዘረ የድሮን ጥቃት በቀል መሆኑ ታውቋል፡፡
በድሮን ጥቃቱ 3 የአሜሪካ ወታደሮች ሲገደሉ በርካቶች ደግሞ እንደተጎዱ ዘገባው አስታውሷል፡፡
ለዚህ አፀፋ ራሷ ኢራንም ብትሆን እንድትመታ ፕሬዘዳንት ጆ ባይደን ከሪፖሊካዊው የፖለቲካ ማህበር ቱባዎች ጫና እንደበረታባቸው ተሰምቷል፡፡
በሶማሊያ ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውል ስስ የእቃ መያዣ ፌስታል ሊከለከል ነው፡፡
ስስ ፌታሎችን ማስመጣት ፣ ማምራትም ሆነ ጥቅም ላይ ማዋል በአገሪቱ ሙሉ በሙሉ እንደሚከለከል አናዶሉ ፅፏል፡፡
ከልከላው ፌስታሎቹን አምርቶ ወደ ውጭ መላክንም ይጨምራል ተብሏል፡፡
የሶማሊያ የአካባቢ ጥበቃ ሚኒስቴር ለአንድ ጊዜ ብቻ ጥቅም ላይ የሚውሉ ፌስታሎች ክልከላው ከመጪው ሰኔ ወር አንስቶ ሙሉ ለሙሉ ስራ ላይ ይውላል ማለቱ ተሰምቷል፡፡
በአገሪቱ ስስ ፌስታሎች ከፍተኛዎቹ የአካባቢ ብክለት አስከታዮች እየሆኑ መምጣታቸው በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
ክልከላው በዚህ ቁስ ምክንያት እየደረሰ ያለውን አካባቢያዊ ብክለት ለመቀነስ ያግዛል ተብሏል፡፡
የኔነህ ከበደ
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comments