ጥር 28፣2016 - የሚነሱ ችግሮችን በንግግር እና በንግግር ብቻ ለመፍታት መንግስታቸው ጽኑ ፍላጎት አንዳለው ጠ/ሚ ዐቢይ አህመድ ተናገሩ
- sheger1021fm
- Feb 6, 2024
- 1 min read
በአማራ ክልል የሚነሱ ችግሮችን በንግግር እና በንግግር ብቻ ለመፍታት መንግስታቸው ጽኑ ፍላጎት አንዳለው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ተናገሩ፡፡
የአማራ ህዝብ ጥያቄ ‘’የልማት፣ የህገ መንግስት ማሻሻያ እንዲደረግ እና የወሰን ይገባኛል’’ መሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ አንስተዋል፡፡
በአብዛኛዎቹ የአማራ ክልል ዞኖች ከክልሉ ነዋሪዎች እና ተወላጆች ጋር የመነጋጋር እድል አግኝቼ ነበር ያሉት ዐቢይ አህመድ የክልሉ ህዝብ ጥያቄዎች የልማት፣ የህገ መንግስት ማሻሻል እና የወሰን ጥያቄዎች መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡
‘’መንግስት በአማራ ክልል የሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ ብዙ ርቀት ሄዷል፤ ለአብነትም 2 .4 ቢሊዮን ብር አውጥተን በዓባይ ወንዝ ላይ በአይነቱ ልዩ የሆነ ድልድይ ገንብተናል’’ ሲሉ አስረድተዋል፡፡
በጎርጎራ ፕሮጀክት አማካኝነትም የክልሉን ቱሪዝም የሚያነቃቃ ስራ ተከናውኗል ብለዋል፡፡
በአገራዊ የምክክር ኮሚሽን በኩል ሌሎች ጥያቄዎች ምላሽ እንዲያገኙ ይሰራል ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ህገመንግስትን በተመለከተ ሁሉም የሚስማማበት ህግ መንግስት እንዲኖር አካታች ሀገራዊ ምክክር ተቋቁሟል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
ይህ እንዲሆን የተፈለገውም ምክንያትም የደርግ መንግስት ሲመጣ የንጉሱን ህገመንግስት ቀዶ እንዳጣለዉ እንዳይሆን ኢህአዴግ ሲመጣም የደርግን ቀዶ እንደጣለዉ እንዳይሆን ነዉ ማለታቸዉ ተሰምቷል፡፡
የሚነሳውን የወሰን ጥያቄን በተመለከተ መንግስት በውይይትና ዘላቂ ሰላም በሚያመጣ አግባብ እንዲፈታ በጽኑ ይፈልጋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡
‘’ከግጭት የምናተርፈው አንዳች ነገር የለም፤ ይልቁንም ያለንን እናጎድላለን ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሰላማዊ ንግግር እና ውይይትን በማስቀደም የትኛውንም ጥያቄ መፍታት እንችላለን’’ ሲሉ ተደምጠዋል፡፡
በክልሉ የሚነሱ ችግሮችን በንግግር እና በንግግር ብቻ ለመፍታት መንግስታቸው ጽኑ ፍላጎት አንዳለው የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አሁንም መንግሰት ለሰላም ንግግር ዝግጁ ነው ብለዋል፡፡
የሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Telegram: https://tinyurl.com/yc6tfzsw
Tiktok: https://bit.ly/44Dd6Il
Comentários