የኢትዮጵያ ፌደራል ፖሊስ በተያዘው በጀት ዓመት በ6 ወራት ውስጥ በአዲስ አበባ እና በሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች የደረሰ 103 የእሳት ቃጠሎ መንስኤዎችን በፎረንሲክ ምርመራ አርጊያለሁ ብሏል፡፡
ፖሊስ አደረኩት ባለው የፎረንሲክ ምርመራም 50 የሚሆኑት ቃጠሎች የደረሱት በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር ምክንያት፣ 11ዎቹ በመካኒካል ችግር፣ 10ሩ ሆን ተብሎ በሰው አማካኝነት የደረሱ፣ 17ቱ በቸልተኝነት የደረሰ እንደሆነ እና 15 ደግሞ በሌሎች ምክንያቶች የደረሱ ቃጠሎ መሆናቸውን ፌዴራል ፖሊስ ባደረኩት ምርመራ አረጋግጫለሁ ብሏል፡፡
ባለፈው ጥቅምት ወር ላይ በአዲስ አበባ መርካቶ ሸማ ተራ ተከስቶ የነበረው የእሳት አደጋ በዚሁ ምርመራ ውስጥ እንደተካተተም ፖሊስ በሪፖርቱ ይፋ አድርጓል፡፡
በምርመራውም የሸማ ተራ የእሳት አደጋ በኤሌክትሪክ ቴክኒክ ችግር የተከሰተ መሆኑን በምርመራው ማጣራት ችያለሁ ብሏል፡፡

ባለፉት 6 ወራት በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 96 እና በክልሎች ደግሞ 7 እንደ ሀገር 103 የእሳት ቃጠሎ አደጋዎች መድረሳቸውን ፖሊስ ተናግሯል፡፡
በዚህም በ582 መኖሪያ ቤት፣ በ12 ተሽከርካሪዎች ፣ በ1965 የንግድ ቤቶች ፣ በስድስት ፋብሪካዎችና የተለያዩ ድርጅቶች በቃጠሎ ምክንያት ጉዳት ስለመድረሱ ከኢትዮጵያ ፌዴራል ፖሊስ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡
በሪፖርቱ ሆን ተብሎ 10 ቃጠሎ ተፈፅሟል ቢባልም ለምን አላማ? እነማንስ ወንጀሉን ፈፀሙት? በህግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ወይ? የሚለውን የፌዴራል ፖሊስ አላብራራውም፡፡
በተመሳሳይ በሌሎች ምክንያቶች የደረሰ 15 ቃጠሎዎችን በተመለከተ በሌሎች ምክንያቶች ሲባል ምን ማለት እንደሆነ በሪፖርቱ አልተብራራም፡፡
እኛም ከላይ ያነሳናቸው ሀሳቦች ዝርዝር ምላሽ እንዲያገኙ በፌዴራል ፖሊስ በኩል ምላሽ እንዲሰጠን ብንጠይቅም ምላሽ ለመስጠት ግን ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡
ፍቅሩ አምባቸው
Comments