top of page

ጥር 6፣2017 – የባህር ማዶ ወሬዎች


በአሜሪካ የሎስ አንጀለሱን የሰድድ እሳት መቆጣጠር የተቻለው 14 በመቶውን ብቻ ነው ተባለ፡፡


የከተማዋ ከንቲባ ካረን ባስ አሁንም አጣዳፊ የሰደድ እሳት መከላከያ ዝግጅት ያሻናል ማለታቸውን ቢቢሲ ፅፏል፡፡


በሎስ አንጀለስ አጣዳፊ የሰደድ እሳት መከላከያ ዝግጅት ያሻል የተባለው ጠንከር ያለ ነፋስ እንደሚከሰት በመተንበዩ ምክንያት መሆኑ ታውቋል፡፡

በካሊፎርኒያው የሰደድ እስከ ትናንት የ24 ሰዎች ሕይወት አልፏል ተብሏል፡፡


23 ሰዎች ደግሞ የደረሱበት እንዳልታወቀ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡


ያም ሆኖ በሎስ አንጀለስ ከትናንት አንስቶ ብዙዎቹ ተማሪዎች ወደ ትምህርት ቤቶቻቸው መመለስ ይችላሉ መባሉ ተሰምቷል፡፡



የሱዳን መንግስት ጦር በጀዚራ ግዛት የምትገኘውን የታምቡል ከተማን በእጄ አስገባኋት አለ፡፡


ቀደም ብሎ ጦሩ የጀዚራ ግዛት ማዕከል የሆነችውን ዋድ ማዳኒን ተቆጣጥሬያታለሁ ማለቱን ሚድል ኢስት ሞኒተር ፅፏል፡፡


ጦሩ የግዛቲቱ 2ኛ ከተማ የሆነችውን ታምቡልን የተቆጣጠረው ከRSF ፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች ጋር ከተደረገ ውጊያ በኋላ ነው ተብሏል፡፡


ለመንግስት ጦር በጀዚራ ግዛት በ48 ሰዓታት ውስጥ 2ኛ ድሉ መሆኑ ተጠቅሷል፡፡


ዝርዝሩ ባይብራራም የሱዳን መንግስት ጦር በታምቡል በRSF ላይ መጠነ ሰፊ ሰብአዊ እና ቁሳዊ ውድመት አድርሼበታለሁ ማለቱ ተሰምቷል፡፡


በዚህ ጉዳይ ከፈጥኖ ደራሽ ሀይሉ በኩል የተሰማ አስተያየት የለም፡፡


ተፋላሚዎቹ ጦርነት ማካሄድ ከጀመሩ አመት ከ9 ወራት ሆኗቸዋል፡፡



የጋዛው የተኩስ አቁም እውን ወደ መሆኛው እየተቃረበ ነው ተባለ፡፡


የጋዛው የተኩስ አቁም እውን መሆኛው በእጅጉ መቃረቡን ለጉዳዩ ቅርበት ያላቸው እና በስም መጠቀስ ያልፈለጉ አራት የአሜሪካ ሹሞች መናገራቸውን ስክሪፕስ ድረ ገፅ ፅፏል፡፡


ድርድሩ የታጋቾች እና የእስረኞች ልውውጥንም የተመለከተ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡


የእስራኤል ጦርም ከጋዛ የመውጫው ጉዳይ የድርድሩ አካል ነው ተብሏል፡፡


ድርድሩ እርምጃ እየታየበት ነው ቢባልም መቼ ሊቋጭ ይችላል የሚለው የጊዜ ሰሌዳ በትክክል አልታወቀም፡፡


ሐማስ እስራኤል የጋዛ ዘመቻዋን አቁማ ወታደሮቿን ካላስወጣች ታጋቾቹን ለመልቀቅ እቸገራለሁ እያለ ነው፡፡


እስራኤል በሐማስ ድንገት ደራሽ ከተፈፀመባት በኋላ የጋዛ የጦር ዘመቻዋን ከጀመረች ከአመት ከ3 ወራት በላይ ሆኗታል፡፡



ሕንድ ከባንግላዴሽ ጋር በሚያዋስናት ድንበር የመከላከያ የግንብ አጥር ለማስገንባት መነሳቷ ሁለቱን አገሮች እያወዛገበ ነው፡፡


እንደሚባለው ሕንድ በሁለቱ አገሮች ወሰን 5 ስፍራዎች የመከላከያ ግምብ የማሳጠር እቅድ አላት፡፡


ውጥኑን ባንግላዴሽ በጥብቅ እየተቃወመችው መሆኑን NDTV ፅፏል፡፡


ባንግላዴሽ የህንድ የድንበር ላይ አጥር ቀዳሚ ስምምነቶቻችንን የሚጥስ ነው ባይ ነች፡፡


የባንግላዴሽ የቀድሞዋ ጠቅላይ ሚኒስትር ሼክ ሐሲና ባለፈው ነሐሴ ወር በገጠማቸው ሕዝባዊ እንቢታ ከአገር ሸሽተው ህንድ ከገቡ በኋላ የሁለቱ አገሮች ግንኙነት እየደፈረሰ መምጣቱ ይነገራል፡፡


አዲሱ የባንግላዴሽ መንግስት ሼክ ሐሲና ከሕንድ ተላልፈው እንዲሰጡት ተደጋጋሚ ጥያቄ እያቀረበ ነው፡፡


የኔነህ ከበደ

Comments


bottom of page