top of page

ጥር 9፣ 2015- የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት በፈቃዳቸው ስራ ለቀቁ


የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት እና ምክትል ፕሬዚዳንት በፈቃዳቸው ስራ ለቀቁ፡፡


በምትካቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በእጩነት ያቀረባቸው ግለሰቦች ሹመት በሕዝብ እንደራሴዎች ምክር ቤት ፀድቋል፡፡


በመሆኑም ወ/ሮ መአዛ አሸናፊና ምክትል ፕሬዚዳንት የነበሩት አቶ ሰለሞን አረዳን ተክተው አቶ ቴዎድሮስ ምህረት ከበደ እና ወ/ሮ አበባ እምቢአለ መንግስቴ ተሹመዋል፡፡


ፕሬዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ በግል ጠበቃነት እየሰሩ የቆዩ መሆናቸውን ሰምተናል፡፡


በተጨማሪም በተለያዩ ተቋማት ነገረ ፈጅ ሆነው ሲሰሩም ቆይተዋል፡፡


በሌላ በኩል ምክትል ፕሬዝዳንት ሆነው ሹመታቸው የፀደቀላቸው ወ/ሮ አበባ እምቢአለ መንግስቴ በተለያዩ ፍርድ ቤቶች በዳኝነት ሲያገለግሉ የቆዩ መሆናቸውና በአሁኑ ጊዜ በጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ሆነው ሲያገለግሉ እንደነበር ሰምተናል፡፡


የእጩዎቹ ሹመት ከመፅደቁ በፊት ለአስተያየት ምክር ቤቱ አጠር ያለ ውይይት አድርጓል፡፡

በተሿሚዎች ስም ዝርዝር ቀድሞ ለምክር ቤቱ አባላትና ለህዝቡም ይፋ መደረግ እንደነበረበትና ሕዝብን የሚያገለግሉ ተሿሚዎችን ሹመታቸው ከመፅደቁ በፊት ስለ ስራ ብቃታቸው አውቀን አስተያየት ለመስጠት ይመቸን ነበር የሚል አስተያየት ተሰጥቷል፡፡


በሌላ በኩል ሀላፊነታቸውን በገዛ ፈቃዳቸው ስለመልቀቃቸው በደፈናው ከሚነገር ይልቅ በምን ምክንያት ለቀቁ የሚለውንም በግልፅ ለምን አይነገረንም? የሚል ጥያቄ ቀርቧል፡፡


የእጩዎቹን የሹመት የውሳኔ ሀሳብ ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የመንግስት ረዳት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ ቤልጅጌ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡


የእጩዎች ለፓርላማው የቀረበበት መንገድ በህገ መንግስት መሰረት የቀረበ መሆኑን የተናገሩት አቶ ተስፋዬ ቤልጅጌ፤ በምን ምክንያት ለቀቁ ለሚለው ጥያቄ ግን ግልፅ የሆነ ምላሽ አልሰጡም፡፡


የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዚዝዳንት ሆነው የተሾሙት አቶ ቴዎድሮስ ምህረት በ3 ድምፅ ተአቅቦ እና በ292 የድጋፍ ድምፅ ሹመታቸው ፀድቋል፡፡


የምክትል ፕሬዚዳንቷ ወ/ሮ አበባ እምቢአለ ደግሞ በሙሉ ድምፅ ሹመታቸው ፀድቆ ሁለቱም ቃለ መሐላ ፈፅመው ሀላፊነታቸውን ተረክበዋል፡፡


የጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት የነበሩት አቶ ሰለሞን አረዳ በመንግሥታቱ ድርጅት የክርክር ፍርድ ቤት የግማሽ ጊዜ ዳኛ ሆነው መሾማቸው ይታወሳል፡፡


ትዕግስት ዘሪሁን


ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…

Comments


bottom of page