ጥር 9፣ 2015የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬቺፕ ታይፕ ኤርዶአን ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል መሆን ካሻቸው
- sheger1021fm
- Jan 17, 2023
- 1 min read

የቱርኩ ፕሬዝዳንት ሬቺፕ ታይፕ ኤርዶአን ስዊድን እና ፊንላንድ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል መሆን ካሻቸው በአሸባሪነት የተፈረጁ ግለሰቦችን አሳልፈው ሊሰጡን ይገባል አሉ፡፡
ቱርክ ሁለቱ አገሮች 130 ያህል ተፈላጊዎችን አሳልፈው እንዲሰጧት እንደምትሻ ኤርዶአን ተናግረዋል፡፡
አንካራ በአሸባሪነት የፈረጀችው የኩርዶች የጦር እና የፖለቲካ ድርጅት PKK ዋነኛ አቀላጣፊዎች ተላልፈው ሊሰጡኝ ይገባኛል ባይ እንደሆነች ዴይሊ ሳባህ ፅፏል፡፡
ከነዚህም በተጨማሪ ነዋሪነታቸው በአሜሪካ የሆነው የሐይማኖታዊ ምሁሩ ፊቱላህ ጉሌን ተባባሪዎችም ከተፈላጊዎቹ መካከል ናቸው ይባላል፡፡
ፊቱላህ ጉሌን እና ተባባሪዎቻቸው ከዚህ ቀደም በቱርክ ተሞክሮ ለከሸፈው መፈንቅለ መንግስት ስማቸው በተደጋጋሚ በተጠያቂነት ይነሳል፡፡
ሲዊድን እና ፊንላንድ የኔቶ አባላት ለመሆን የቱርክን ጨምሮ የ30ውም የቃል ኪዳን ድርጅቱ አባላት ይሁንታ ያሻቸዋል፡፡
የቱርክ ፓርላማ ሁለቱ አገሮች ተፈላጊዎቹን አሳልፈው ካልሰጡኝ የኔቶ የአባልነት መደገፊያውን አላፅድቅላቸውም እያለ ነው፡፡
የኔነህ ከበደ
ሸገርን ወሬዎች፣ መረጃ እና ፕሮግራሞች ይከታተሉ…
Comments