የካሜሩን መንግስት የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን በፕሬዘዳንት ፖል ቢያ ጤንነት ጉዳይ እንዳያወሩም ሆነ እንዳይፅፉ ከለከላቸው፡፡
AFP አገኘሁት ያለው ሰነድ መሰረት ፖልቢያ በአሁኑ ወቅት በጠና መታመማቸውን እንዳረጋገጠ TRT አፍሪካ ፅፏል፡፡
የ91 አመቱ የካሜሩን አረጋዊ መሪ ከህዝብ እይታ ከራቁ መቆየታቸው ይነገራል፡፡
በዚሁ ጉዳይ በአገሪቱ ወሬ እና ጉምጉምታው በርትቷል ተብሏል፡፡
የካሜሩን መንግስት በበኩሉ መገናኛ ብዙሃኑ ስለ ፖል ቢያ ጤንነት ጉዳይ እንዳይፅፉም ሆነ እንዳያወሩ በብርቱ አስጠንቅቋቸዋል፡፡
ትዕዛዙን የሚተላለፉትን በህግ እጠይቃቸዋለሁ ብሏል፡፡
ፖል ቢያ ካሜሩንን ለ41 አመታት በፕሬዘዳንትነት እየመሩ ነው፡፡
በአፍሪካም ለብዙ አመታት በአገር መሪነት ከቀጠሉት መካከል አንዱ ሆነው ይጠቀሳሉ፡፡
ሩዋንዳ ከፍተኛ የደም መፍሰስ አስከታዩን የማርበርግ ወረርሽኝ እየተቆጣጠረችው ነው ተባለ፡፡
አገሪቱ ወረርሽኙን እየቆጣጠረችው ስለመሆኑ ማረጋገጫ የሰጠው የአፍሪካ የበሽታዎች መከላከያ እና መቆጣጠሪያ መስሪያ ቤት (Africa CDC) እንደሆነ አሶሼትድ ፕሬስ ፅፏል፡፡
ወረርሽኙ በአገሪቱ ከተከሰተ ካለፈው 2 ሳምንት ወዲህ 13 ሰዎችን ገድሏል ተብሏል፡፡
አገሪቱ በሙከራ ደረጃ ላይ ያለውን የማርበርግ መከላከያ ክትባት ስራ ላይ እያዋለች መሆኑ በመረጃው ተጠቅሷል፡፡
ክትባቱ ለግንባር ቀደም የጤና ባለሙያዎች እና በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ቅርበት ለነበራቸው መሰጠቱ ታውቋል፡፡
የሩዋንዳን ወረርሽን የመገደብ ጥረት ያደነቀው አፍሪካ CDC አገሮች ዜጎቻቸው ወደ ሩዋንዳ እንዳይጓዙ ማከላከላቸውን እንዲያቆሙ መጠየቁ ተጠቅሷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እስራኤል አለም አቀፍ ሕግን እየጣሰች ነው ሲል ከሰሰ፡፡
ድርጅቱ በእስራኤል ላይ ክሱን ያሰማው የእስራኤል ጦር በደቡባዊ ሊባኖስ የሚገኝን የድርጅቱን ሰላም አስከባሪዎች ይዞታ ካጠቃ በኋላ እንደሆነ ቢቢሲ ፅፏል፡፡
እንደሚባለው የእስራኤል ጦር የሰላም አስከባሪዎቹን የጥበቃ ስፍራ በታንክ ደብድቧል፡፡
በውጤቱም ሁለት ሰላም አስከባሪ ወታደሮች አካላዊ ጉዳት እንደገጠማቸው ታውቋል፡፡
የሊባኖስ መንግስት እስራኤል በደቡባዊ ሊባኖስ በፈፀመችው የአየር ድብደባ 5 የጤና ባለሙያዎችን ገድላብኛለች የሚል ክስ አሰምቷል፡፡
ሔዝቦላህም ወደ ሰሜናዊ እስራኤል ሮኬቶችን መተኮሱን እንደቀጠለ በዘገባው ተጠቅሷል፡፡
እስራኤል ሁለት ሰላም አስከባሪዎችን አቁስላለች ስለመባሉ እንዲህም ነው እንዲያም ነው ያለችው ነገር የለም፡፡
ቱርክሜንስታን የሩሲያውን ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲንን አስራ ለአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት(ICC) አሳልፋ እንድትሰጥ በዩክሬይን ተጠየቀች፡፡
ፑቲን ከዛሬ ጀምሮ የማዕከላዊ እስያዋን ቱርክሜንስታንን እንደሚጎበኙ አናዶሉ ፅፏል፡፡
የሩሲያው ፕሬዘዳንት በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት (ICC) የመያዣ ትዕዛዝ ካወጣባቸው ቆይቷል፡፡
ትዕዛዙ ከወጣባቸው በኋላ ፑቲን በተለያዩ አገሮች ጉብኝት አድርገዋል፡፡
ከመያዣ ትዕዛዙ መውጣት በኋላ ፑቲን በተጓዙባቸው አገሮች ልያዞት ብሎ የሞከረ አገር የለም፡፡
ሩሲያ በአለም አቀፉ የወንጀል ችሎት የቀረበባትን ውንጀላ ታስተባብላለች፡፡
የኔነህ ከበደ
Comments